በኮንዶሚኒየም ዕጣ አወጣጥ ጋር በተያያዘ በወንጀል የተጠረጠሩ 8 አመራሮችና የሶፍትዌር ባለሙያዎች ፍርድ ቤት ቀረቡ

አርብ ሐምሌ 8 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ከ14ኛው ዙር 20/80 እና የ3ኛ ዙር የ40/60 የአ/አ ከተማ ኮንዶሚኒየም ቤቶች ዕጣ አወጣጥ ሥነ ሥርዓት ላይ ያልቆጠቡና በወቅቱ ያልተመዘገቡ 172 ሺህ ግለሰቦችን ያላግባብ እንዲካተቱ በማድረግ፤ ህዝብ በመንግስት ላይ እምነት እንዳይኖረው አድርገዋል ተብለው የተጠረጠሩ 8 አመራሮችና የሶፍትዌር ባለሙያዎች በዛሬው ዕለት በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 1ኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀርበዋል።

በተጠረጠሩበት ወንጀል ፍርድ ቤት የቀረቡት ተጠርጣሪዎች፤ የቴክኒክ ሙያ ስልጠና አይሲቲ ቢሮ ም/ቢሮ ሀላፊ አብርሐም ሰርሞሌ፣ የቤቶች ልማት ዳታ ቤዝ ቡድን መሪ ስመኘው አባተ እና የሶፍትዌር ባለሙያዎች ሀብታሙ ከበደ፣ ዮሴፍ ሙላት፣ ጌታቸው በሪሁን፣ ቃሲም ከድር፣ እንዲሁም የቤቶች የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ሚኪያስ ቶሌራ እና የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን አይሲቲ ሀላፊ ኩምሳ ቶላ ናቸው።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል መርማሪ ተጠርጣሪዎች በኮንዶሚኒየም ዕጣ አወጣጥ ላይ ያልተመዘገቡ ያልቆጠቡ ግለሰቦችን በማካተት፣ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማስገኘት በማሰብና ህዝብ በመንግስት ላይ እምነት እንዲያጣ ለማድረግ 172 ሺህ ያልቆጠቡ ግለሰቦችን ሥም በዳታ ቤዝ እንዲካተቱ አድርገዋል ሲል የተጠረጠሩበትን መነሻ ለችሎት አቅርቧል።

79 ሺህ በተገቢው መንገድ የቆጠቡ ግለሰቦች በዕጣው መካተታቸውን ከባንክ መረጃ የቀረበ ሲሆን ቀሪው 172 ሺህ ግን ያልቆጠቡና ያልተመዘገቡ ግለሰቦች መካተታቸውን ከባንክ ከቀረበው ሲስተም ተረጋግጧል ብሏል ፖሊስ።

ሂሳባቸውን የዘጉና የወጡት ግለሰቦችን ኹሉ እንዲገቡ ተደርጎል ያለው መርማሪ፤ በተለይም የ2005 ተመዝጋቢዎችን ወደ 97 ተመዝጋቢዎችን በማስገባት ጭምር ዕጣው እንዲሰረዝ እና ከፍተኛ ኪሳራ እንዲደርስ ተደርጓል ሲል ፖሊስ ለችሎቱ ገልጿል።

በተጨማሪም የለማው ሶፍትዌር ከሰው ንክኪ የፀዳ እንዳልነበር አስረድቷል።

ተጨማሪ ምርመራ ሥራ ለማከናወን ማስረጃ ለመሰብሰብ እና የምስክር ቃል ለመቀበል ተጨማሪ የ14 ቀን ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል።

ተጠርጣሪ አብርሐም ሰርሜሎ በበኩላቸው፤ እኔ የቴክኒክ ሙያ ስልጠና አይሲቲ ቢሮ ም/ል ሀላፊ ሆኜ ስሰራ ሶፍትዌር አልምተን 5 ጊዜ በኢኖቬሽን ሚኒስቴር እንዲፈተሽ አድርገናል ያሉ ሲሆን፤ ክቡር ከንቲባዋም በተገኙበት በህዳር 1 ቀን ተፈትሾ ብቁ መሆኑና ዳታ ቤዙ ምንም እንደሌለው ተረጋግጦ ነው ወደሥራ የገባነው ሲሉ አስረድቷል።

ኢንሳን ማረጋገጫ እንዲሰጠን ጠይቀን ምላሽ ሳይመጣ ቀርቷል ያሉት አብርሀም፤ እኛ ስለቁጠባ አያገባንም ሥራችን ሶፍትዌር ማልማት ብቻ ነው ሲሉም ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በተጨማሪም በዕጣ አወጣጥ ወቅት ሶፍትዌሩ ታይቶ፣ ዳታ ቤዙ ምንም እንደሌለው ተረጋግጦ “ሀክ” እንዳይደረግ እንኳን ኢንተርኔት አጥፍተን ነው የገባነው ሲሉም አስረድተዋል።

አብርሐም በወንጀሉ ተሳትፎ እንደሌላቸው ገልጸው፤ በተቋማቸው በለማው የሶፍትዌር ልማት ሥራ መንግስትን ከወጪ በማስቀረት ተግባር መፈጸማቸውን በመጥቀስ ዋስትና እንዲፈቀድላቸው ፍድ ቤቱን ጠይቀዋል።

ሌላኛው የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን አይሲቲ ሀላፊ ኩምሳ ቶላ በበኩላቸው፤ 60 ወር የቆጠቡትን 20/80 ቆጣቢዎች የካቲት 14 ወደ ሲስተም ማስገባታቸውን ገልጸው፤ የ40/60 ብቁ ቆጣቢዎችን ደግሞ በየካቲት 21 ቀን መረጃውን ወደ ሲስተም እንዲገባ አድርገናል ብለዋል።

እንደ አጠቃላይ ሂሳብ ከፍቶ የቆጠበም ያልቆጠበም፤ እንዲሁም በባንክ ሂሳቡን የዘጋ ሰው ኹሉ ዳታ ቤዝ ውስጥ እንዲገባ እንደሚደረግ አብራርተዋል።

ሥራው ሲሰራ ምንም ችግር አለው ብዬ አልወስድም ያሉት ኩምሳ፤ ዋስትና ተፈቅዶልን በውጭ ሆነን ጉዳያችንን እንከታተል ሲሉ የዋስ መብታቸው እንዲጠበቅ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።

ቀሪ ተጠርጣርጣሪዎችም በየሥራ ተሳትፏቸው ምንም ወንጀል እንዳልፈጸሙ ገልጸው፤ የቤተሰብ አስተዳዳሪ በመሆናቸውን ፍርድ ቤቱ ተገንዝቦ የዋስት እንዲፈቅድላቸው ጠይቀዋል።

ጉዳያቸውን የተከታተለው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ፤ መዝገቡን መርምሮ ትዕዛዝ ለመስጠት ለፊታችን ሰኞ ለሐምሌ 11 ቀን ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱን ጋዜጠኛ ታሪክ አዱኛ ከችሎት ዘግባለች።

Source: Link to the Post

Leave a Reply