በኮንጎ 131 ሲቪሎች ተገድለዋል ሲል ተመድ አስታወቀ

https://gdb.voanews.com/10060000-0aff-0242-2e70-08da5a27464e_w800_h450.jpg

ኤም-23 የተሰኙት ታጣቂዎች ባለፈው ወር በምሥራቅ ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ቢያንስ 131 ሲቪሎችን መጨፍጨፋቸውን፣ ከሁለት ደርዘን በላይ አስገድዶ መድፈር መፈጸማቸውን የቅድም ምርመራ ውጤቶች ማሳየታቸውን በአገሪቱ የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ልዑክ አስታውቋል። 

መንግስት አማጺያኑ ባለፈው ወር 300 የሚሆኑ ሲቪሎችን ገድለዋል ሲል ክስ አቅርቦ ነበር። 

የኤም-23 ቡድን ግድያውን መፈጸሙን በመካድ፣ ስምንት ሲቪሎች ግን በተባራሪ ጥይት መሞታቸውን ያምናል። 

በኮንጎ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ልዑክ የሆነው ሞኑስኮ ትናንት ማምሻውን እንዳስታወቀው 131 ሰዎች የተገደሉት “በሲቪሎች ላይ በተፈጸመ ቂም በቀል ነው” ብሏል። 

ሞኑስኮ በተጨማሪም ምርመራው የተካሄደው የዓይን ምስክሮችን በማናገር እንጂ ግድያ በተፈጸመበት ሥፍራ በተደረገ ማጣራት ባለመሆኑ፣ የሟቾች ቁጥር ከተጠቀሰውም በላይ ሊሆን ይችላል ብሏል።

ሟቾቹ 102 ወንዶች፣ 17 ሴቶችና፣ 12 ሕጻናት ሲሆኑ፤ በጥይትና በቢላ መገደላቸውን የሞኑስኮ ሪፖርት አመልክቷል ሲል ኤ.ኤፍ.ፒ ዘግቧል። 

ስምንት ሰዎች በጥይት ሲቆስሉ፣ 60 የሚሆኑ ታግተዋል። ቢያንስ 22 ሴቶችና 5 ልጃገረዶች አስገድዶ መድፈር ተፈጽሞባቸዋል ሲልም ሞኑስኮ በሪፖርቱ አስታውቋል። 

 

Source: Link to the Post

Leave a Reply