
በወለጋ አከባቢ የመንግስት አንቡላንሶች ለኦነግ የመሳሪያ አቅርቦት አገልግሎት እየሰጡ መሆኑ ተገለጸ፡፡ አሻራ ሚዲያ ህዳር፡-30/03/13/ዓ.ም ባህር ዳር በወለጋ አከባቢዎች የመንግስት አንቡላንሶች ለኦነግ የመሳሪያ አቅርቦትና ለኦነግ አመራሮች እንዲሁም ለኦነግ የመረጃ ክፍል ወታደሮች የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል። እንደምንጫችን ገለጻ አንቡላንሶቹ በቀላሉ እንዳይለዩ ታርጋቸውን በመፍታት ይንቀሳቀሳሉ። በተለይም ደግሞ በሌሊት ጊዜ ታርጋቸውን ፈትተው ለኦነግ አገልግሎት ሲሰጡ ያድራሉ ሲሉ የመረጃ ምንጫችን ገልጸውልናል። በአካባቢው የምንኖርና የአንቡላንስ አገልግሎት የምንጠይቅ ተገልጋዮች አገልግሎቱን በምንጠይቅበት ወቅት ስራ ላይ ናቸው የሉም የሚል ምላሽ እየተሰጠን ለብዙ ጉዳት ተዳርገናል ሲሉም ነዋሪዎች ለአሻራ ሚዲያ ተናገረዋል። ለዚህ ማሳያ ደግሞ ባለፈው ሰሞን ሊሙ እርቁንቢ የሚባል ቦታ ላይ የተገደሉ አማራዎችን የመራው የኦነግ ክፍል በአንቡላንስ እየተንቀሳቀሰ ግድያውን መፈጸሙን አውስተዋል። ስለሆነም በወለጋ አካባቢ ለህዝብ አገልግሎት እንዲውሉ የተመደቡ አንቡላንሶች በአሁኑ ስዓት ህዝብን ከማገልገል ይልቅ ለአጥፊ ቡድኖች መደበቂያና መጓጓዣ መሆናቸውን ምንጫችን ጠቁመዋል፡፡ በተጨማሪም በወለጋ አካባቢ ንጹሀን የሚጨፈጨፉባቸው የተለያዩ የጥፋት መሳሪያዎች የሚገቡት በአካባቢው በሚገኙ በመንግስት አንቡላንሶች እንደሆነም ተናገረዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ወላዶችና አስቸኳይ የህክምና እርዳታ የሚፈልጉ የአካባቢው ነዋሪዎች ችግር ላይ መሆናቸውም ተመላክቷል፡፡ በመጨረሻም መንግስት ወደ አካባቢው በመግባት ለህዝብ የተመደቡ አንቡላንሶች የጥፋት ቡድኑን በመተው ህዝቡን እንዲያገለግሉ ማድረግ አለበት ሲሉ ነዋሪዎች መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ዘጋቢ፡-ጥላሁን ታምሩ
Source: Link to the Post