በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ የተፈጠረውን የውሃ እጦት ለማቃለል የከተማው የእሳት ማጥፍያ ቦቴዎች ለዜጎች ውሃ እያሰራጩ እንደሚገኙ ኢትዮ ኤፍ ኤም ከከተማው ነዋሪዎች ያገኝው መረጃ ያመላክታል፡፡
የህዝቡ የውሃ ችግር በቀላሉ የሚፈታ እንዳልሆነ የገለጹት ነዋሪዎቹ፣ ለልብስ እና ለእቃ ማጠብያ የሚሆን ውሃ ከከተማው እሳት እና አደጋ ጽ/ቤት እየቀረበልን ነው ብለዋል፡፡
አንድ የከተማዋ ነዋሪ በስልክ እንደነገሩን፣ ላለፉት ሁለት ቀናት በከተማው የእሳት አደጋ መከላከያ ቦቴ አማካኝነት ውሃ ማግኝታቸውን ነግረውናል፡፡
ከዚሁ የንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ጋር በተያያዘ ከሰሞኑ የከተማው ነዋሪዎች ሰልፍ ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን ይህን ተከትሎም የዜጎች ሕይወት ማለፉ ይታወቃል፡፡
መንግስት በወልቂጤና አካባቢው ለበርካታ ወራት የተቋጠውን የውሃ አቅርቦት ችግር በዘላቂነት መፈታት ሳይችል መቅረቱን የተናገሩት ነዋሪዎቹ አሁንም ትኩረት ይሰጠን ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
በተለያዩ ጊዜያት በወልቂጤ የውሃ ፕሮጀክት ሥም ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ ሀብት በግለሰቦች፣ በመንግሥት ባለሥልጣናት እና በተደራጁ ቡድኖች ሲመዘበር መቆየቱ ነዋሪዎቹ ያነሳሉ፡፡
በመሆኑም መንግስት ለዞኑ ለውሃ ፕሮጀክት ተብሎ የሚመደበውን ሃብት በመቆጣጠር ለታለመለት አላማ ብቻ ይውል ዘንድ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡
የጉራጌ ዞን አስተዳደር የወልቂጤ ከተማ የውሃ ጽ/ቤት ሃላፊ በዚህ ጉዳይ ዙርያ ማብራርያ እንዲሰጡን ተደጋጋሚ ሙከራ ያደረግን ቢሆንም ልናገኛቸው አልቻልንም፡፡
ኢትዮ ኤፍ ኤም ከአካባቢው ከከተማዋ ነዋሪዎች ባገኝው መረጃ መሰረት፣ ከሰሞኑ አለመራጋጋት ጋር በተገናኝ መደበኛ እንቅስቃሴ አሁንም እንዳልተጀመረ ተናግረዋል፡፡
በሔኖክ ወ/ገብርኤል
የካቲት 14 ቀን 2015 ዓ.ም
ለተጨማሪ መረሃዎች የቴሌግራምና የዩቲዩብ ቻናሎቻችንን ይቀላቀሉ!
Telegram https://t.me/ethiofm107dot8
YouTube https://www.youtube.com/@onelovebroadcast
ያሎትን አስተያየት እና ጥያቄ በአጭር መልዕክት 6321 ላይ ይላኩልን።
ከኛ ጋር ስለሆናችሁ ከልብ እናመሰግናለን።
Source: Link to the Post