
በወልድያ በህወሓት የወረራ ጦርነት ወቅት ጉዳት ለደረሰባቸዉ ትምህርት ቤቶች ከሰባት ሚሊዬን ብር በላይ የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ የካቲት 17 ቀን 2015 ዓ/ም … አዲስ አበባ ሸዋ ክርስቲያን ሪሊፍ ከተባለ ድርጅት በተገኘ ከሰባት ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ቁሳቁስ በህወሓት የወረራ ጦርነት ምክንያተ ጉዳት ለደረሰባቸዉ ትምህርት ቤቶች የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ድጋፍ ማድረጉን ገልጧል። የወልድያ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ሰለሞን አበጋዝ የክርስቲያን ሪሊፍ ድርጅት ከዚህ በፊት ለጤና ተቋማት ድጋፍ ማድረጉንና አሁንም በድጋሜ በጦርነት የተጎዱ ተቋማትን በመለየት ለስድስት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ ለአንድ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትና ለአንድ ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጅ ከሰባት ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው ወንበር፣ ጠረንጴዛና ሸልፍ ድጋፍ ማድረጉን ገልፀዋል፡፡ የወልደያ ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ምክትል ሀላፊ አቶ ተስፋማርያም ይመር ዩኒቨርሲቲው ከአሁን በፊትም የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርግ እንደነበር ገልፀዉ አሁንም የወንበር፣ ጠረንጴዛና ሸልፍ ቁሳቁሶችን ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡ ድጋፉ የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንዳለዉና በአንደኛና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የምርምር ስራወችን ለመስራት የኮምፒዩተር፣ የቤተ ሙከራ እቃዎችና ኬሚካሎች እጥረት በመኖሩ የሚመለከታችሁ አካላት ድጋፍ እንድታደርጉ ሲሉ አቶ ተስፋማርያም ጥሪያቸዉን አስተላልፈዋል፡፡ የቆቦ ከተማ ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጅ ዋና ዲን አቶ ደሳለኝ አደም ኮሌጁ ሙሉ በሙሉ የወደመ መሆኑንና የንድፈ ሀሳብ ስልጠና ለመስጠት በችግር ዉስጥ እንደነበሩ ገልፀው አሁን የተደረገዉ ድጋፍ ከስራ ማቆም ወደ ስራ ማስጀመር የሚወስድ ነው ብለዋል። ዩኒቨርሲቲዉ ከዞኑና ከወረዳ አስተዳደሮች ጋር በመነጋገር ከመማር ማስተማሩ ባሻገር የህብረተሰቡን ችግር ሊፈቱ የሚችሉ የምርምር ስራዎችን እየሰራ ነዉ፡፡ ሰሜን ወሎ ኮሙኒኬሽን
Source: Link to the Post