You are currently viewing በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከባልደራስ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ ጥር05/2014/አሻራሚዲያ/ ከሁሉ አስቀድመን፣ በየጦር ግንባሩ “ ኢትዮጵያ ሀገሬ አትፈርስም ” ብለው ቤት ንብረቸውን ጥለው ዘምተው፡-…

በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከባልደራስ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ ጥር05/2014/አሻራሚዲያ/ ከሁሉ አስቀድመን፣ በየጦር ግንባሩ “ ኢትዮጵያ ሀገሬ አትፈርስም ” ብለው ቤት ንብረቸውን ጥለው ዘምተው፡-…

በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከባልደራስ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ ጥር05/2014/አሻራሚዲያ/ ከሁሉ አስቀድመን፣ በየጦር ግንባሩ “ ኢትዮጵያ ሀገሬ አትፈርስም ” ብለው ቤት ንብረቸውን ጥለው ዘምተው፡- 1. የህይወት መስዋዕትነት ለከፈሉት፣ 2. ለቆሰሉት፣… 3. በአሁኑ ሰዓት በየቀበሮ ጉድጓዱ ሀገር እየጠበቁ ለሚገኙት የመከላከያ፣ የዐማራና እና የአፋር ልዩ ኃይሎች፣ ፋኖዎች እና ሚሊሺያዎች፣ 4. ከላይ ለተዘረዘሩት መስዕዋትነት ለከፈሉ አካላት ሁሉ ደጀን የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብን ከልብ እናመሠግናለን፡፡ ዘማቾች፣ እንደ አባት አያቶቻችሁ ሀገር እየጠበቃችሁ፣ እያስቀጠላችሁ ነውና፣ ስማችሁ በታሪክ መዛግብት በወርቅ ቀለም ተጽፎ ይኖራል፣ 5. የባልደራስ አመራሮችና አባላት በፈጠራ ክስና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሳቢያ በእስር በነበሩበት ጊዜ ከጎናቸችን ላልተለዩት የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ለእውነትና ለሙያቸው ለታመኑ ሚዲያዎች፣ ለሀገር ውስጥ እና ለዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብት ተቋማት፣ 6. እንዲሁም፣ የባልደራስ አመራርን ከእስር እንዲፈቱ ለማድረግ በተካሄዱት የተለያዩ ተግባራት ለተሳተፉ ለባልደራስ አባላት፣ በውጭ ሀገር ላሉት የባልደራስ ድጋፍ ሰጭ ድርጅቶች (ቻፕተሮች) እና ለባልደራስ ደጋፊዎች በሙሉ ልባዊ ምሥጋና እናቀርባለን፡፡ ለእውነት ስለቆማችሁ ልትኮሩ ይገባል፡፡ ወደ ሰሜን ግንባሮች ጉዞ አገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ የህልውና ትንቅንቅ ላይ ትገኛለች፡፡ ከዚህ አኳያ፣ ባልደራስ የአገር ወዳዶች ስብስብ እንደመሆኑ መጠን ለአገር መቀጠል የበኩሉን አስተዋፅኦ እያደረገ ይገኛል፡፡ በዚህ ረገድ፣ ግንባር ድረስ በመሄድ የተለያዩ ድጋፎችን አድርጓል፡፡ አሁን ደግሞ፣ ከእስር የተፈቱት የባልደራስ አመራር አባላት በአፋር እና በአማራ ክልል ወደሚገኙት የተወሰኑ ግንባሮች በአካል በመሄድ መስዕዋትነት ለከፈሉት እና እየከፈሉ ለሚገኙት ምሥጋና እንዲያቀርቡ፣ የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን ጎብኝተው እንዲያጽናኑ የድርጅታችን ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ወስኗል፡፡ በዚሁ መሠረት ከአርብ፣ ጥር 6/2014 ዓ.ም ጀምሮ እንቅስቃሴ ይጀምራሉ፡፡ የሰሜኑን ጦርነት እና የእነ ስብሃት ነጋን ክስ መዝገብ መቋረጥን በሚመለከት የሰሜኑ ጦርነት መነሻው ህወሓት በጀመረው ቅድመ-ማጥቃት እንደሆነ ፓርቲያችን ይረዳል፡፡ የፌደራል መንግሥቱ በርካታ የአፈፃፀም ችግሮች ቢኖሩበትም፣ ያደረገው የመከላከል ጦርነት ፍትሃዊ እንደሆነ እናምናለን፡፡ በዚሁ መሠረት፣ ፓርቲያችን ፖለቲካዊ ድጋፍ ከማድረጉም በተጨማሪ፣ ቦታው ድረስ በመሄድ ቁሳዊ እገዛዎች አድርጓል፡፡ ሆኖም፣ መንግሥት “ምዕራፍ አንድ” ያለውን ዘመቻ የኢትዮጵያን ሉኣላዊነት ሳያረጋግጥ ማቆሙ ትልቅ አደጋ ያዘለ መሆኑን ገምግመናል፡፡ ዘመቻውን ያቆመበትን አመክንዮ ከማስረዳት አኳያም ሆነ፣ እርሱን ተከትሎ ከህዝብ በሚነሳው ተጨባጭ ስጋት ዙሪያ በቂ ምላሽ አልሰጠም፡፡ መንግሥት “ተከድተናል” ለሚለው የኢትዮጵያ ህዝብ እያሳየ ያለው ንቀት መስተካከል ይገባዋል፡፡ ህወሓት አሁንም የአገሪቱን አንድነት ሊፈታተን በሚችል ወታደራዊ ቁመና ላይ ይገኛል፡፡ የዘመቻው ፍጻሜ የኢትዮጵያን አንድነት አደጋ ላይ የሚጥለውን የህወሓት ወታደራዊ አቅም በመስበር መቋጨት ይገባል፡፡ እንዲሁም፣ የህወሓት የፖለቲካ እና የጦርነቱ ዋነኛ ቀያሾች የሆኑ፣ ጉዳያቸውን በሕግ ጥላ ስር ሆነው እየተከታተሉ የነበሩ እስረኞችን ሰሞኑን መፍታት መጀመሩ የሕግ የበላይነትን የጣሰ ውሳኔ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ በኢትዮጵያ አስተማማኝ ሠላም ሊገኝ የሚችለው መንግሥት ተጠያቂነትንና ፍትህን ሲያሰፍን ብቻ ነው፡፡ ይህን መርህ በተቃራኒ መልኩ የሚደረግ ማናቸውም ቁማር አገርንና ህዝብን መልሶ ወደ ችግር እንደሚከት አያጠያይቅም፡፡ ከዚህ አንፃር፣ ገዢው ፓርቲ በጦርነቱ የተጎዱትን አግልሎና ራሱን ብቸኛ የጉዳዩ ባለቤት አድርጎ፣ ተጠያቂነትና ፍትህን ባላሰፈነ ሁኔታ ክስ ለማቋረጥ የሰጠው ውሳኔ የፖለቲካም ሆነ የሞራል ተቀባይነት የለውም፡፡ ስለሆነም፣የባልደራስ አመራር አባላትን ጨምሮ፣ በመንግሥት በኩል የሚደረጉ ክስ መቋረጦች ተጠያቂነትና ፍትህን ባገናዘበ መልኩ እንዲሆን ፓርቲያችን ጥሪውን ያቀርባል፡፡ ከተቋረጡት ክሶች ጋር በተያያዘ በሕዝቡ ዘንድ የተነሳው ተቃውሞ፣ ከተጠያቂነትና ከፍትህ አኳያ እንጂ፣ ከቂም በቀል እና ከጥላቻ አለመሆኑን ግልጽ ሊሆን ይገባል፡፡ የሰሞኑ የብልጽግና ፓርቲ ውሳኔ፣ ኢትዮጵያዊነት ጎልቶ የተንፀባረቀበትን የፀረ-ህወሓት ህዝባዊ አንድነት አቋምን ቀጣይነት የሚያሳጣ እና የኢትዮጵያን ፖለቲካ የሚያወሳስብ ነው፡፡ ይህ ህጋዊነትን ያልተላበሰ ውሳኔ አገሪቱን ግልጽ ለሆነ አደጋ አጋልጧል፡፡ የባልደራስ አመራሮች ክስ መቋረጥን በተመለከተ የባልደራስ አራት አመራሮች ከሰኔ 24/2012 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ታህሳስ 29/2014 ዓ.ም. ድረስ፣ “የእስር በእርስ ጦርነት እንዲነሳ አድርገዋል፤” እንዲሁም፣ “የሽብር ወንጀል ለመፈፀም ተሰናድተዋል” በሚሉ ሁለት የፈጠራ ክሶች ለአንድ ዓመት ተኩል በእስር ከተንገላቱ በኋላ ተለቀዋል፡፡ አሁን ላይ ደግሞ፣ 5 የባልደራስ አባላት——ሰላም ታደለ፣ ምትክ ካሣሁን፣ ዮርዳኖስ እንዳለ፣ ፋሲል ውሂብ፣ ብሩክ ጫኔ——በአስቸኳይ አዋጁ ተይዘው ለአንድ ወር ከሶስት ሳምንታት በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ አባላት ለእስር የተዳረጉት በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት በእስር የነበሩ የትግል አጋሮቻቸውን ጠይቀው ሲወጡ ነበር፤ የፓርቲያችን አባላት ከመሆን ባለፈ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አልጣሱም፡፡ የባልደራስ አመራር አባላት በእስር ቆይታቸው ለመንግሥት በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ ባስተላለፏቸው መልዕክቶች፣ በፈጠራ ክስ ከመከሰሳቸው አኳያ፣ የእድሜ ልክ እስር እንኳን ቢፈረድባቸው፣ የይቅርታ እና የምህረት ጥያቄ እንደማያቀርቡ እና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መለቀቅ እንዳለባቸው በግልጽ ቋንቋ ተናግረዋል፤ መንግሥትም ይሄንን በግልጽ ያውቃል፡፡ የባልደራስ አመራር አባላት ታህሳስ 29/2014 ዓ.ም. ማታ ከእስር እንዲለቀቁ ተደርገዋል፡፡ ፍቺው ድንገተኛ እና ያልተጠበቀ ነበር፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ላለፉት አራት ወራት ከመንግሥት ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ምንም ዓይነት የመልዕክት ልውውጥ አልነበረም፡፡ የድርጅታችን አባላት በፈጠራ ክስ እየተወነጀሉ መታሰራቸው በኢትዮጵያ መሠረታዊ ለውጥ እንደሌለ፣ ማንኛውም ዜጋም በተመሳሳይ መንገድ ለእስር መዳረግ እንደሚችል የሚያመላክት በመሆኑ፣ ድርጊቱን መላው ህዝብ ሊያወግዘው ይገባል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም ቢሆን፣ የፖለቲካ ቂም መወጣጫ መሆን ስለማይገባው፣ በባልደራስ ላይ ለበቀል የተወሰደው ህገ-ወጥ እርምጃ ተቀልብሶ ከላይ የተጠቀሱት አምስቱ አባላት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከእስር እንዲለቀቁ በጥብቅ እናሳስባለን፡፡ በአጠቃላይ፣ በሀሰት የተከሰሱት አመራሮቻችንን እና አባሎቻችንን በሚመለከት፣ መንግሥት ይቅርታ ጠይቋቸው፣ ካሣ ሊከፍላቸው ይገባል፡፡ በክሱ ሂደት በተጨባጭ እንደታየው፣ በመንግሥት በኩል አንድም ሚዛን የሚደፋ ማስረጃ አልቀረበም፡፡ እውነታውን ህዝብ ያውቀዋል፡፡ የምክክር ኮሚሽኑን እና ሂደቱን በተመለከተባልደራስ የአገራችን ፖለቲካዊ ጥያቄዎች በውይይት እና በምክክር፣ የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት፣ እንዲሁም፣ በስር ነቀል ለውጥና መፈታት እንዳለበት ያምናል፡፡ ከዚህ አንፃር፣ የብሔራዊ ምክክር ሂደቱ ለፖለቲካ ቁማር ሳይውል ውጤታማ እንዲሆን እንታገላለን፡፡ በዚህም መሠረት፣ በምክክር ኮሚሽኑ ለመሳተፍ የሚፈልጉ የፖለቲካ ኃይሎች፣ ሲቪክ ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በሙሉ ሁለት ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት ይገባቸዋል፡፡ እንጠይቃለን፡፡ እነዚህም፡- 1. የኢትዮጵያ አንድነትን እና ሉዓላዊነትን ማስቀጠል ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መቀበል፣ 2. በሠላማዊ መንገድ መንቀሳቀስን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መቀበል የሚሉት ናቸው፡፡ ፓርቲያችን የእስከ አሁኑን ጉዞ ገምግሞ፣ ተከታዮቹን ምክረ ሃሳቦች ያቀርባል፡- 1. የምክክሩ ባለቤት ህዝብ፣ የፖለቲካ ኃይሎች እና የሲቪክ ተቋማት እንጂ፣ አንድ ፓርቲ ከ90% በላይ አብላጫ ወንበር የያዘበት ፓርላማ ስላልሆነ፣ ሂደቱን ሁሉም ባለድርሻዎች በባለቤትነት የሚመሩበት ሁኔታ መፍጠር፤ 2. የምክክር ሂደቱ ግልጽ፣ ተዓማኒ እና ከገዢው ፓርቲ ተጽዕኖ ነጻ እንዲሆን ማድረግ፣ 3. የምክክር ሂደቱን ግልጸኝነት ለመፍጠር የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በታዛቢነት እንዲጋበዙ የሚሉት ናቸው፡፡ በመጨረሻም፣ ድርጅታችን ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ የገዥው ፓርቲ ብርቱ ብትር ሲያርፍበት ቆይቷል፡፡ ያለምንም ማጋነን፣ምንም ፋታ አግኝቶ አያውቅም፡፡ ይህም ሆኖ ግን፣ የድርጅታችን አባላት ቁርጠኝነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንጂ እየላላ አልሄደም፡፡ በዚህ መሠረት፣ ትግላችንን ከመቼውም በላይ አጠናክረን የምንቀጥል መሆኑን ከአብራኩ ለፈለቅነው የኢትዮጵያ ህዝብ እናረጋግጣለን፡፡ የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ጥር 05/2014 አዲስ አበባ

Source: Link to the Post

Leave a Reply