በዋግህመራ ብሄረሰብ አስተዳደር በድርቅ ምክንያት የ6 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተነገረ፡፡

በዋግኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር በሰሃላ ሰየምት ወረዳ የሚገኙ ከ50ሺህ በላይ ነዋሪዎች ለድርቅ መጋለጣቸው ተገልጧል፡፡

ድርቁ በ26 ቀበሌዎች የተስፋፋ ሲሆን እስካሁንም 6 ሰዎች ህይወታቸው ማለፉ ተገልጿል።

በዋግኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ስር በሚገኘዉ የሰሃላ ሰየምት ወረዳ ዉስጥ የሚገኙ አስራሶስት ቀበሌዎች ዉስጥ የሚኖሩ ከ50ሺህ በላይ ነዋሪዎች ለድርቅ መጋለጣቸውን ኢትዮ ኤፍ ኤም ሰምቷል፡፡

በዋግኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ምህረት መላኩ ከጣቢያችን ጋር በነበራቸዉ ቆይታ እንደነገሩን፤ በወረዳዉ በአስራ ሶስት ቀበሌዎች እንዲሁም በአበርገሌ 6 እና በዝቋላ ባሉ 7 በአጠቃላይ 26 ቀበሌዎች ላይ ድርቅ ተከስቷል፡፡

ወደ 8ሺህ13 ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኖ ነበር ያሉት ሀላፊው አሁን ላይ ግን ሙሉለሙሉ ምርት የለውም ብለውናል።

ከምርቱ ባሻገር ደግሞ የእንስሳት መኖ እጥረት በማጋጠሙ ፤ ከፍተኛ ቁጥር ያለው እንስሳ መኖ ፍለጋ እየተሰደደ መሆኑን አንስተዋል።

በመኖ እጥረት ምክንያትም ከ1ሺህ 2መቶ በላይ የቁም እንስሳት መሞታቸውንም ነግረውናል።

ሰሃላ ሰየምት ወረዳ ችግሩ በከፍተኛ ደረጃ በመባባሱ በጣም ፈጣን ምላሽ የሚፈልግ ነው ያሉት አቶ ምህረት፤ ሁለቱ ወረዳዎች በከፊል በመጎዳታቸው እና ከአጎራባች ክልሎችም ድጋፍ በማግኘታቸው እጥረቱ ቢኖርም ወደ ከፋ ችግር ውስጥ ግን አልገቡም ብለዋል።

ከክልሉ መንግስት እና ከፌደራል በአጠቃላይ ወደ 1ሺህ 5መቶ ኩንታል አከባቢ እህል በድጋፍ ቢገኝም ሌላ መፍትሄ እስኪገኝ ግፋ ቢል ለአንድ ወር የሚያቆይ እንጂ ከዛ የዘለለ አይሆንም ነው ያሉት።

ሃላፊው አክለውም የተሰጠው ድጋፍ አበርገሌን ሳይጨምር ለሰሃላ ሰየምት እና ለዝቋላ ወረዳዎች የደረሰ ቢሆንም በሁለቱ ወረዳዎች ካለው ፍላጎት አንፃር 50 በመቶውን እንኳን መድረስ አልቻልንም ሲሉ ተናግረዋል።

በእስከዳር ግርማ

ጥቅምት 13 ቀን 2016 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply