በውጭ ምንዛሪ ቀጥታ ክፍያ መቀበል የሚቻልበት ስርዓት ይፋ ተደረገ  

ሦስተኛዋ የዓለም የዲፕሎማሲ መናኻሪያ ወደ ሆነችው ኢትዮጵያ የሚመጡ በርካታ ጎብኚዎች እና ዲፕሎማቶች የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ በአግባቡ ለማግኘት ያስችላል የተባለ በኪው አር ኮደ (QR code) የሚሰራ የክፍያ ስርዓት ይፋ ተደረገ። 

የክፍያ ስርዓቱን የቪዛ ኩባንያ፣ አቢሲንያ ባንክ እና ትረስትድ ቴክ የግል ድርጅት ለሦስት ያበለጸጉት ሲሆን ጎብኚዎች እና ዲፕሎማቶች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ይዘውት ከሚመጡት ገንዘብ 80 በመቶ የሚሆነውን ይዘውት የሚመለሱ መሆኑ የክፍያ ስርዓቱ ዋና መነሻ እንደሆነ የቴክኖሎጂ አበልጻጊው የትረስትድ ቴክ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሐብታሙ ታደሰ ገልጸዋል። 

አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በቀን እስከ 10 ዶላር ድረስ የሚከራዩ ክፍሎች ያሏልቸው ሆቴሎች ጭምር እንደሚገኙ የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ ቱሪዝም እና ሆቴል ማርኬት ማሕበር ፕሬዝዳንት ጌታሁን ዓለሙ ናቸው። ነገር ግን በርካቶቹ ቪዛ እና ማስተርካርድን የመሳሰሉ ፈጣንና ከንክኪ ነጻ የሆኑ የክፍያ ስርዓቶች ሳይሆን በጥሬ ገንዘብ የሚጠይቁ መሆኑንም የማሕበሩ ፕሬዝዳንት ገልጸዋል። 

ዛሬ የክፍያ ስርዓቱ ይፋ በተደረገበት ወቅት ዋና ሥራ አስኪያጁ እንደገለጹት ጎብኚዎችና ዲፕሎማቶች ገንዘብ እንዳያወጡ ትልቁ ምክንያት በክሬዲት ካርድ መክፈል አለመቻላቸው ነው ብለው በርካታ ባንኮች አገልግሎቱን ለትላልቅ ተቋማት ብቻ የሚያቀርቡ በመሆኑ አገልግሎቱ ውስን እንደሆነ ጠቅሰዋል። 

ከነገ ጀምሮ በአዲስ አበባ የሚካሄደውን የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ በዋናነት ታሳቢ ተደርጎ ይፋ የተደረገው የክፍያ ስርዓት የሕብረቱ ጉባዔ ከተጠናቀቀ በኋላም በማንኛውም ጊዜ እና የንግድና አገልግሎት ዓይነቶች ላይ የሚቀጥል መሆኑን አዲስ ማለዳ ማወቅ ችላለች። 

የኢትዮጵያ ቱሪዝም እና ሆቴል ማርኬት ማሕበር ፕሬዝዳንት “ሆቴሎቻችን ለሚያጡት የውጭ ምንዛሪ በተመለከተ ትልቅ መፍትሔ ይዞ መጥቷል” የተባለውን የክፍያ ስርዓት የአፍሪክ ሕብረት ጉባዔን ያገናዘበ በመሆኑ በፍጥነት በአዲስ አበባ የሚገኙ የማሕበሩ አባላት እንዲጠቀሙት ጥሪ አቅርቧል። 

አዲስ ማለዳ የክፍያ ስርዓቱ ተደራሽነትን በተመለከተ ለትረስትድ ቴክ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሐብታሙ ታደሰ ላቀረበችው ጥያቄ፤ “ከትንሽ እስከ ትልቅ ቢዝነሶች በሙሉ ነው በዚህ ስርዓት ውስጥ እንዲገቡ የምንፈልገው” ብለዋል። በተጨማሪም እስከ የካቲት 7 ቀን 2016 ድረስ 25 ሆቴሎች አገልግሎቱን መጠቀም መጀመራቸውን ለአዲስ ማለዳ የገለጹት ሥራ አስኪያጁ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ 2 ሺህ 500 ሆቴሎችን ሁሉ ለማዳረስ እቅድ የተያዘ ቢሆንም የአፍሪካ ሕብረት ጉባዔን ታሳቢ በማድረግ አዲስ አበባ ላይ ተጀመሯል ብለዋል።  

የቱሪዝም እና ሆቴል ማርኬት ማህበር ፕሬዝዳንት ይህ የኪው አር ኮድ ክፍያ ስርዓት ዓለም አቀፍ የክፍያ አማራጮችን ያካተተ መሆኑ ጥሩ ያደርገዋል ብለው ማህበሩ በአፍሪካ ሕብረት ጉባዔ ሂደት ውስጥ መቀመጫ ያለው በመሆኑ ዲፕሎማቶችና የአገራት መሪዎችን በቅርበት በማግኘት ይህንን እናበረታታለን ሲሉ ገልጸዋል።

ተመሳሳይ የክፍያ ስርዓቶች ውስጥ በስፋት “አይገኝም” የተባለው ለሠራተኞች ጉርሻ (ቲፕ) የመስጫ ሁኔታ የተመቻቸለት የክፍያ ስርዓቱ፤ እስካሁን አብረው የሚሰሩ ተቋማት የሠራተኞች ጉርሻ ተሰብስቦ ድርጅቱ የሚያካፍልበት ስርዓትን የሚከተሉ በመሆናቸው ጉርሻው (ቲፕ) ወደ ተቋሞቹ ሒሳብ ገቢ እንደሚሆን ማወቅ ተችሏል። 

ይሁን እንጂ ጉርሻ ወደ ሠራተኞች የግል ሒሳብ ገቢ እንዲሆን ለሚፈቅዱ የንግድ ተቋማትና አገልግሎት አቅራቢዎች ይኸው አገልግሎት ዝግጁ እንደሆነ የትረስትድ ቴክ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሐብታሙ ታደሰ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። በስልክ ካሜራ ኪው አር ኮድ (QR code)ን በመቅረጽ ብቻ የሚሰራው የክፍያ ስርዓቱ፤ ከጉርሻ (ቲፕ) በተጨማሪ ገንዘብ የተወሰነም ሆነ ሙሉ ለሙሉ ተመላሽ ማድረግ የሚያስችል እንዲሁም የንግድ ባለቤቶች የገንዘብ ዝውውሩን የሚከታተሉበት እንደሆነ ተገልጿል። 

ብዙ ሚልየን ብሮች ፈሰስ እየተደረገበት ነው የተባለው የክፍያ ስርዓት ዓለም አቀፍ የመጨረሻ ጥራቱን የጠበቀ የደሕንነት ደረጃ እንዳለው የተገለጸ ሲሆን ሌሎች ባንኮችም ከቪዛ ኩባንያ ጋር እንዲሰሩ በማድረግ በቅርቡ ሌሎች ባንኮችም በዚህ የክፍያ ስርዓት እንደሚጠቀሙ ይጠበቃል። 

በተለይ የዲፕሎማቶች ጊዜ የተጣበበ በመሆኑ እና በካርድ መክፈል ባለመቻላቸው በርካታ ገንዘብ ተመልሶ ይወጣል፤ ይህንን ማስቀረት የሚችል የክፍያ ስርዓት መሆኑ የተገለጸ ሲሆን የንግድ ባለቤቶች በውጭ ምንዛሪ የሚደረገውን ግብይት መከታተል በመቻላቸው በተቋማት ላይ የውጭ ምንዛሬውን በባንክ ተመን ተቀብለው ለእራሳቸው በጥቁር ገበያ መንዝረው የሚጠቀሙ ሠራተኞች በማስቀረት ነጋዴዎች እና አገሪቱ ማግኘት የሚገባቸውን እንዲያገኙም ያስችላል ተብሏል።  

Source: Link to the Post

Leave a Reply