በዐቢይ ፆም ወቅት ሰላም፣ ፍቅር፣ ይቅር ባይነት መታዘዝና አካፍሎ መብላትን መተግበር እንደሚገባ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ገለፁ፡፡

አዲስ አበባ፣የካቲት 29፣ 2013 በዐቢይ ፆም ወቅት ሰላም፣ ፍቅር፣ ይቅር ባይነት መታዘዝና አካፍሎ መብላትን መተግበር እንደሚገባ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ገለፁ፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በዐቢይ ፆም ወቅት ሰላም፣ ፍቅር፣ ስምምነት፣ ይቅር ባይነት መታዘዝና አካፍሎ መብላትን ምዕመኑ መተግበር እንደሚገባው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ፓትርያርኩ የዐቢይ ጾም መግባትን ምክንያት በማድረግ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በመግለጫቸውም “የዐቢይ ፆም ዋና ዓላማ ዲያብሎስን በመቃወም ለእግዚአብሄር መገዘት ነው” ብለዋል፡፡ “በሌላ አገላለጽ እግዚአብሔር በቅዱስ መጽሐፍ አድርጉ ያለንን ማድረግ፤ አታድርጉ ያለንን አለማድረግ ነው፤ ይህም ለእግዚአብሔር መገዛት ማለት እንደሆነ ማስተዋል ይገባልም” ነው ያሉት፡፡

በጾሙ ወቅትም ሰላም፤ ፍቅር፤ ስምምነት፤ ይቅር ባይነት፤ መታዘዝ ፤መተጋገዝና መራራት ካለው አካፍሎ መብላትን ምዕመናኑ አብዝቶ ሊተገብረው እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ በኢትዮጵያ እየተከሰተ ያለው ረሃብ እርዛት እና መፈናቀል ቤተክርስቲያኗን እያሳሰባት መሆኑን ገልፀው “ይህም በመካከላችን ፍቅርና ሰላም በመጥፋቱ” መከሰቱን ጠቁመዋል፡፡ ለችግሩ መፍትሄ ለመስጠትም በሰላምና በፍቅር ሁሉም ወገን ያለሰለስ ጥረት ማድረግ ይኖርበታል ብለዋል፡፡ በየአካባቢው የተቸገሩ ወገኖችን ለመርዳትና ለማገዝ እንዲሁም የሃይማኖት ተቋማትና በጎ አድራጊዎች
በችግር ያሉ ወገኖችን በመደገፍ የበኩላቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply