
በዓለ መርቆሪዎስ የደብረ ታቦር እና የአካባቢው መገለጫ እንዲኾን እየሠራ መኾኑን የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ጥር 24 ቀን 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ሸዋ በዓለ መርቆሪዎስ የደብረ ታቦር እና የአካባቢው መገለጫ እንዲኾን እየሠራ መኾኑን የደብረ ታቦር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ደሳለኝ በላቸው ተናግረዋል። የታሪክ ፣የባሕል፣ የሃይማኖት ፣የፀና ኢትዮጵያዊነት እና የጀግንነት ማሕደር የኾነችው ደብረታቦር የብዙ ታሪኮችና ቅርሶች መገኛ ናት። ከተማዋ በውስጧ ታሪካዊ እና መንፈሳዊ ሀብቶችን አቅፋ ይዛለች። በዙሪያ ገባዋም በበርካታ ታሪካዊ እና መንፈሳዊ ሥፍራዎች ተከባለች። ደብረ ታቦር በወርኃ ጥር ጥምቀትና በበዓለ መርቆሪዎስ ትደምቃለች። ሁለቱ በዓላት በከተማዋ በልዩ ድምቀት ይከበራሉ፣ በበዓላቱም በርካታ እንግዶች ወደ ከተማዋ ይገባሉ። ደብረታቦር በዓለ መርቆሪዎስን ለማክበር ዝግጅቷን ጨርሳ እንግዶቿን እየተቀበለች ነው። የከተማዋን ቅድመ ዝግጅት በተመለከተ ለአሚኮ የተናገሩት የደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ደሳለኝ በላቸው ከተማዋ በሁሉም ረገድ ዝግጅቷን ጨርሳ እንግዶቿን እየተቀበለች ነው። ቅድመ ዝግጅታቸው በሂደትም በውጤትም ስኬታማ መኾኑን ገልጸዋል። ከተማዋ በፀጥታው ፣በሆቴል ዝግጅት እና በሌሎች ዝግጅቶች በቂ ዝግጅት አድርጋ እንግዶቿን እየተቀበለች መኾኗንም አስታውቀዋል። እንግዶችን በኢትዮጵያዊነት ባሕል እየተቀበልን ነውም ብለዋል። ከአበው የቆዬው በዓል ዘንድሮ ከወትሮው በተለዬ መንገድ ይከበራልም ነው ያሉት። በዓለ መርቆሪዎስ የደብረ ታቦር እና የአካባቢው መለያ እንዲኾን እየሠሩ መኾናቸውንም አስታውቀዋል። የአካባቢው ማኅበረሰብ መንግሥትነትን የሠራ፣ ሥርዓትን የሚያከብር፣ የሚያስከብር፣ በሕግ አምላክ ሲባል እንኳን ሰው ወንዝ ይቆማል ብሎ የሚያምን መኾኑንም አንስተዋል። ባሕልና ማንነት የሚገለጽበት ፣ ታሪክ የሚዘከርበት ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የሕዝብ ሥነ ልቦና የሚገለጽበት፣ ልማት ከፍ የሚልበት ነውም ብለዋል። የመርቆሪዎስ በዓል ባሕል የሚገለጽበት፣ ሃይማኖት የሚጸናበት፣ ሀብት የሚመነጭበት ዘርፍና ብዙ ጥቅም ያለው መኾኑንም ተናግረዋል። የከተማ አሥተዳደሩ የመርቆሪዎስ በዓል በየጊዜው እያደገና የበርካታ እንግዶች መዳረሻ እንዲኾን በትኩረት እንደሚሠራም አስታውቀዋል። ባሕል እንዲሁም በዓል እንደሌላው ዘርፍ መመራትን ይጠይቃል ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በትኩረት በመምራት ከፍ እንዲል እናደርጋለን ነው ያሉት። ከተማዋ በመሠረተ ልማት የተሻለች እንድትኾን በትኩረት እንደሚሠሩም አስታውቀዋል። ከተማዋ ታሪኳን የሚመጥን መሠረተ ልማት ያስፈልጋታልም ብለዋል። ከተማዋ የቱሪስት መዳረሻ የመኾን በርካታ እድሎች አሏት ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው እድሉን በአግባቡ እንጠቀማለንም ብለዋል። ዘገባው የአሚኮ ነው።
Source: Link to the Post