በዓመት ከ14ሺህ በላይ ለሚሆኑ አቅም ለሌላቸው ተከሳሾች ጠበቃ እየቀረበላቸው እንደሚገኝ ተነገረ፡፡

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተከላካይ ጠበቆች ጽ/ቤት ክስ ተመስርቶባቸው ጠበቃ ቀጥረው መከራከር ለማይችሉ አካላት የጥብቅና አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

በዚህም በየአመቱ የተከላካይ ጠበቆች ጽ/ቤት ከ14ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የጥብቅና አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጧል፡፡

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተከላካይ ጠበቆች ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ደሳለኝ ከበደ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንደተናገሩት፣ ለየትኛውም የወንጀል ጉዳይ ክስ ለተመሰረተባቸው ዜጎች በነጻ የጥብቅና አገልግሎት እየሰጠን እንገኛለን ብለዋል፡፡

ጽ/ቤቱ የጥብቅና አገልግሎት የሚሰጠው ከአምስት አመት በላይ ሊያስፈርዱ የሚችሉ የወንጀል ጉዳዮች ላይ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ከአምስት አመት በላይ ሊያስፈርዱ የሚችሉ ልክ እንደ እድሜ ልክ ጥፋቶች የሰው ግድያ እንዲሁም ከገቢዎች የደረሰኝ ማጭበርበር ጋር የተያየዙ ወንጀሎች እና በሽብር የተከሰሱ ወንጀሎች ይገኙበታል ሲሉ ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡

መንግስት መክሰስ ብቻ ሳይሆን ለተከሰሱ ሰዎች በራሱ ወጪ ተከላካይ ጠበቃ በመመደብ ፍትህ እንዲያገኙ እያደረገ ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡

ጠንካራ እና የሕዝብ አመኔታ ያተረፈ ፍርድ ቤት የሚገነባዉ በመብቱ ጉዳይ የማይደራደር ተገልጋይ እና በሕግና ማስረጃ መሠረት አሳማኝ ክርክር በማቅረብ ተገልጋዮች ፍትህ እንዲያገኙ ማድረግ የሚችል ተከራካሪ የፍትህ ተቋም ሲኖር መሆኑንም አቶ ደሳለኝ ተናግረዋል፡፡

በሔኖክ ወ/ገበርኤል

ጥር 21 ቀን 2016 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply