በዘረኝነት ጦስ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም ባፍጢሙ ሊደፋ ነው! – ነፃነት ዘለቀ

ፈረንጆቹ  “Jumping from the frying pan into the fire.” የሚሉት ፈሊጣዊ አነጋገር አላቸው፡፡ በኛም አይጠፋም፡፡ “ከድጥ ወደ ማጥ”፣ “ከእሳት ወደ ረመጥ”፣ እንደዚሁም ከደረሰብን ሁለንተናዊ ስቃይና ኢ-ሰብኣዊ ድርጊቶች አኳያ ወያኔን በዚህ መግለጽ የሚበዛበት ቢሆንም “ትሻልን ሰድጄ ትብስን አመጣሁ”ን የመሳሰሉ ፈሊጦችና ምሣሌያዊ አባባሎች አሉን፡፡ ሁኔታዎች በዚህ መልክ ከቀጠሉም – አይበልብን እንጂ – አፈናና እርግጫ እንዲሁም ሌሎቹ ወያኔያዊ የማሰቃያ መንገዶች መከሰታቸው አይቀር ይሆናል፡፡ ይችን ነጥብ ትንሽ ሰፋ አድርገን እንያት መሰለኝ፡፡

ደርግ ሥልጣን ያዘ – በ1967ዓ.ም፡፡ ለውጡ መሬት እስኪረግጥ ድረስ መብት በመብት ሆን፡፡ መናገሩ፣ መጻፉ፣ መሰለፉ… እንደልብ ሆነ፡፡ እነጎሕን፣ እነዲሞክራሲያን… ማስታወስ ይቻላል፡፡ ለውጡ መሬት ሲረግጥ ግን ደረታችን በጥይት መበሳሳትና አፋችን መለጎም በስፋት ቀጠለ፡፡ ማታም ሆነ ጧም ሆነ – ለውጥ አንድ፡፡

ሕወሓት በኢሕአዴግ የመሀል አገር ካባው ሥልጣን ያዘ – በ1983ዓ.ም፡፡ ወዲያው መብት በመብት ሆን፡፡ መናገር መጻፉ በሽ በሽ ሆነ፡፡ እስከጥግ አወራን፤ ተሳደብን፤ ተቆጣን፤ ቦረቅን፤ ተሰለፍን፡፡ አሁን 36 ቢሊዮን ዶላር ዘርፎ ማንም ዝምቡን እሽ የማይለው ዜጋ በአደባባይ ሲገማሸር እንደማናይ ያኔ 20 ብር ጉቦ የተቀበለ የትራፊክ ፖሊስ አሥር አሥር የብር ኖቶች እንደጉትቻ በሁለቱ ጆሮዎች ተለጥፈውበት መሀል አራት ኪሎ ላይ ተረሸነና “እሱን ያዬ ይቀጣ” ተብሎ ተፎከረ፡፡ “ኣሃ! በዚህ ዓይነት ሙስና ከዚች ሀገር ድራሹ ሊጠፋ ነው!” ብለን ተስፋችንን ጣልን፡፡ በሚዲያውም እነጦቢያን፣ እነሩሕን፣ እነሣሌምን፣… ማስታወስ ይቻላል፡፡ የመለስ ዘረኛ አገዛዝ መሬት ሲቆነጥጥ ግን አናታችንን በጥይት ይበሳሱት ገቡ፡፡ ከዚያም አንገታችንን ቀበርን፡፡ በቁም ሞትን፡፡ ማታም ሆነ ጧትም ሆነ – ለውጥ ሁለት፡፡

የለውጡ ባቡር ቀጠለ — “ማታም ሆነ፣ ጧትም ሆነ” መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ደረሰ፡፡ ዶ/ር አቢይ (ሲቆላመጥ አቢቹ) ሥልጣን ያዘ፡፡ አሁን ድረስ በብዙ መብት እንደተንበሸበሽን አለን፤ አጥተን የነበረውን ግን ሊኖረን የሚገባንን ተፈጥሯዊ የመናገርና የመጻፍ መብቶች ስላገኘን አንዳንዶቻችን የደስታው ስካር አሁንም ድረስ አለቀቀንም፡፡ ከዚህ ምን ይቀጥል ይሆን በሚለው ትንቢታዊ አቅጣጫ ማሟረት አልፈልግም፡፡ ይቅርብኝ፡፡ ነገን መጠበቅ ይሻላል፡፡ የተደቀነብን አደጋ መኖሩን ሳልጠቁም ባልፍ ግን አድርባይ ወይም መሀል ሰፋሪ ያስብለኛልና ፈጽሞ አላደርገውም፡፡ የአዲስ አበባ ቢሮዎችና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እንደሚያሳብቁት ከሆነ  የአቢቹ አስምጥ ንግግርና በተግባር የሚታየው ነገር አራምባና ቆቦ ነው – ይህም ለማንም አይበጅም፡፡ 

እናስ ከፍ ሲል የተናገርኩት ስህተት ነው? ኢትዮጵያ መውለድ እንጂ ማሳደግ አትችልም የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ ሾተላይ አለባት፡፡ የአራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ክፍል ተቆጥሮለት ሦስት ሰባት ዓመታትን ያህል (ለ21 ዓመታት) ጠበል ካልተረጨ የሆነ ሰውን የሚለውጥ የጉግማንጉግ መንፈስ ሳይኖርበት አይቀርም፡፡ ወደ ጀመርኩት ….

ዘረኝነት የሚከረፋ የሰው ልጅ ጠላት ነው፡፡ ዘረኝነት ኅሊናን የሚያሳውር እጅግ አደገኛ ነቀርሣ ነው፡፡ ዘረኝነት መድኃኒት ያልተገኘለት በስሜት አምባላይ ፈረስ አስቀምጦ በደመ ነፍስ ሽምጥ የሚያስጋልብ የማኅረሰብና የሀገር ትልቁ ፀር ነው፡፡ ዘረኝነት እስካልተወገደ ድረስ የትኛውም ሕዝብም ሆነ የትኛውም ሀገር በዕድገት ፈቀቅ ሊል አይችልም፡፡ በኛ ሀገር ውስጥ ሕወሓት የተከለው ዘረኝነት አሁን ግዘፍ ነስቶ ሀገሪቷን ሊያጠፋ በቋፍ ላይ እንደሚገኝ የተገነዘብን ወገኖች ብዙ ነን፡፡ በስሜት ባህር የሚዋኙና የለውጡ ምርቃና ያልለቀቃቸው ወገኖች ጭብጨባቸውን ይቀጥሉ፡፡ በደምብ ያጨብጭቡ፡፡ ሲነቁ የእጃቸውን በጭብጨባ መላጥ እያዩ ይጸጻታሉ፡፡ አሁን ግን እንደክርስቶስ ዘመን የስቅሎ ስቅሎ ሰዎች በለውጡና በአቢቹ ፍቅር ይበዱ፡፡ ጭብጨባ ጥሩ ነው፡፡ ጭብጨባ በርባንን ያስፈታል፤ ክርሰቶስን ግን ያሰቅላል፡፡ ጭብጨባ ልብን ያሳብጣል – ሀገርን ግን ያጎብጣል፡፡ ጭብጨባ እውትን ይደብቃል፤ ሀሰትን ግን ያገንናል፡፡ ጭብጨባ በፍቅር ብን ያደርጋል፤ በጎን ግን የጥላቻን ዘር ያፋፋል፡፡እናም እናጨብጭብ!

ትናንት ማታ ነው፡፡ ከጓደኞቼ ጋር እንጫወታለን፡፡ አንደኛው በንግድ ባንክ ይሠራል፡፡ ጉዳችንን ሰማሁና ዕንቅልፍ ባይኔ ሳይዞር አደረ፡፡ አሁን መሥሪያ ቤቴ ስገባ ደግሞ ሌላው ጓደኛየ ሌላ ጉድ ነገረኝ፡፡ ባጭር ባጭሩ ልንገራችሁና እናንተም ትንሽ ተናደዱ፡፡ ግን ጭብጨባውን አትርሱ፡፡ ከምርቃናም (euphoria) እንዳትወጡ አደራችሁን፡፡ ጭብጨባ ብዙ ነገርን ያስረሳል፡፡

አንድ መቶ አካባቢ ቅርንጫፍ ያሉትን በዘር የተዋቀረ አንድ ባንክ በምክትልነት ያስተዳድር የነበረ አንድ “ገመቹ” (ከዘረኛ ሐጎስ ተገላገልን ባልን ማግሥት ሌላ ዘረኛ ገመቹ መጣና ዐረፈው! ወይ የዚች ሀገር ዕድል!) በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና ሰው ሆኖ ተሾመ፡፡ ይህ ከ1300 በላይ ቅርንጫፎች ያሉት የሁላችንም ባንክ የግል ንብረት ይመስል በዘረኝነት ሰንሰለት የተቆላለፉ ሰዎች በአንዴ እየተቆጣጠሩትና ሥራውንም እያበለሻሹት ነው – እንዳገኘሁት የውስጥ መረጃ፡፡ ብዙ ነባርና ከፍተኛ ልምድና ችሎታ ያላቸው የባንኩ ባለሙያዎችም በዚህ ብልሹ ዘረኛ አሠራር በመበሳጨት ሥራቸውን በገዛ ፈቃዳቸው እየለቀቁ ወደ ውጭ ሀገራትና ወደ ግል ባንኮች እየተመሙ ነው፡፡ ባንኩ እየተፍረከረከ ነው፡፡ አየር መንገድና ባንክ ነበሩ እንደምንም እየተንፈራገጡ የኢትዮጵያን ምስል ይዘው የቆዩት፡፡ አሁን ግን በሌላ ሀፍረት የለሾች ሁለቱም በአንዴ ዘጭ እንዳይሉ ሥጋት አለ፡፡ ዘረኝነት እንዲህ ናት!

አንዲት ቀጭን ማሳሰቢያ – ሥራው የሚፈልገውን ዕውቀትና ችሎታ እንዲሁም የትምህርት ደረጃ እስካሟላ ድረስ ባንክንም ይሁን አየር መንገድንና ሌላውን መሥሪያ ቤት ሁሉ የአንድ ነገድ አባላት ሙሉ በሙሉ ቢይዙት ጉዳየ አይደለም፡፡ ይህን የዘረኝነት ደዌ እየተናገርኩ ያለሁትም በዘረኝነት በሽታ ተለክፌ ሳይሆን በዚሁ ደዌ ምክንያት አለምንም ዕውቀትና ችሎታ ሥራና ኃላፊነት ላይ በሚመደቡ ዜጎች ሀገራችን ምን ያህል እየተንገላታች እንደምትገኝ ለመግለጽ ነው፡፡ እመኑኝ – በፍጹም ዘረኛ አይደለሁም፡፡ የኔ ችግር በዘር መክሊት እየተሳሳቡ ያለችሎታና ልምድ፣ ያለ ትምህርትና የሙያ ብቃት ለመጠቃቀም ብቻ – ሌላውንና የሚጠሉትን ወገን ከጥቅምና ከሥራ ለማግለል ብቻ – ሌሎችን ካለማመን በመነጨ የግል ፍላጎትንና ጥቅምን ለማሳደድ ታስቦ ከተከናወነ እጅግ ያበሳጨኛል፤ ያናድደኛል፤ ያመኛልም፡፡ይህን ዓይነት ከእንስሳት የወረደ አሠራርም ማንም ያድርገው እጠየፈዋለሁ፡፡ አምናና ዘንድሮ በዚህ ረገድ አንድ ሆኑ፡፡ “አልሸሹም ዘወር አሉ፡፡” እኔ በሰውነት ብቻ ስለማምን እንጂ ጎሣ ቢኖረኝና የኔ ጎሣ በዚህ መልክ መረን ለቆ ባይ ተመሳሳይ አቋም ነው ያለኝ፡፡ ስለሆነም ንግግሬ አጠቃላይ ነው፡፡ ግን እንኳንስ ጎሣ አልኖረኝ!

ዘረኞች ለጤናማ አሠራር ደንታቢስ ናቸው፡፡ አንድ ሰው በዘሩ ምክንያት አንድ የኃላፊነት ቦታ ላይ ሲመደብ ለተልእኮ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ለዘሮቹ በማድላት የጎሣውን አባላት በዚያ ቦታ ላይ ሆኖ መጥቀም ነው ዋና ዓላማው – ከዚያች ወልጋዳ አካሄድ ዝንፍ አይልም፡፡ ባንክ ከሆነ መሥፈርትን ሳያሟሉ ብድርን መፍቀድ፣ ዕዳን መሰረዝ፣ ገንዘብን ለጎሣዊ ዓላማ ማዋል፣ እርስ በርስ መጠቃቀም … ከተመደበው ዘረኛ የሚጠበቅ የሥራ ግዴታ ነው፡፡ ከዚህ አልፎ በብሔራዊ ስሜት ተመር – ለሁሉም ዜጎች ተጨንቆ – ሌሎችንና ሀገርን ልጥቀም ቢል ከቦታው ይነሳል፡፡ ወደማይረባ ቦታም ይወረወራል፡፡ በርሱ ቦታም ሌላ ዘረኛ ይመደብበታል፡፡

በዚህ መልክ ነው ኢትዮጵያ የጠፋችውና እየጠፋች ያለችው፡፡ ኤቢሲዲን የማያውቅ አምባሳደርና ዲፕሎማት በየሀገሩ እየተመደበ ሀገር የጦጣና የዝንጀሮ መጫወቻ ሆና የምናያት የዘረኝነት አባዜ ባስከተለብን መዘዝ ነው፡፡ እነጎሹ ወልዴንና እንዳልካቸው መኮንንን ያፈራች ሀገር ፀጋየ በርሔን የመሰለ የደናቁርት አለቃ አምባሳደር አድርጋ ስትሾም ከማየት የበለጠ ዘግናኝ ነገር ሊኖር አይችልም፡፡ የመመደቢያው መሥፈርት ጎሣና የወንዝ ልጅነት ሲሆን እነዶክተር አላምረውና ዶክተር ዕቁባይ ቤታቸው ውስጥ ሕጻናትን እያጫወቱ ሲውሉ እነደበሳይና እነደቻሳ ከዘበኝነትም ይሁን ከአትክልተኝነት በቀጥታ ተመዘው በተባበሩት መንግሥታትና በቻይና የኢትዮጵያ ሙሉ ባለሥልጣን አምባሳደር ሆነው ሊሾሙ ይችላሉ – ዋናው በገዢው ዘረኛ መንግሥት መታመናቸው እንጂ ችሎታና ዕውቀታቸው ዜሮና ከዜሮም በታች ቢሆን ምንም ማለት አይደለም፡፡ የትውልድ ዝቅጠትን ለመረዳት ከኢትዮጵያ በላይ ጉልኅ ማስረጃ ሊኖር አይችልም – በተለይ ያለፉት 28 ዓመታትና አሁንም ራሱ፡፡

የሁለተኛው ጓደኛየ መረጃ ደግሞ በየመሥሪያ ቤቱ ስለሚንሳፈፉ አማሮች ነው – ይቺ አማራ ፈርዶባት አሁንም በአዲሱ መንግሥት ልክ እንደክርስቶስ እየተወገረች ናት — ለበጎ ነው ግን፤ ታዲያንም መጨረሻዋን ሳታዩ እርግማን አይቅደማችሁ፡፡ በብዙ መሥሪያ ቤቶች ልምድና ችሎታው እያላቸው ሲያቀብጣቸው አማራ ሆነው በመፈጠራቸው ብቻ ከሥራ እየተባረሩ መሆናቸውን መረዳት የሚቻልበት ሁኔታ  ተፈጥሯል – ለዚህ ተግባር ክንውንም “ከላይ ወደታች የወረደ አቅጣጫ ተቀምጧል” ነው የሚባለው ያለ – በወያኔ ቋንቋ፡፡ ቸር ክራሞት፡፡

Leave a Reply