በዘንድሮ የአገው ፈረሰኞች በአል 3ሺህ ፈረሰኞች ይሳተፋሉ፡፡

በ2015 አመት በበአሉ የተወዳደሩ ፈረሰኞች ቁጥር ከ6ሺህ በላይ እንደነበረ ተገልጻል፡፡

ዘንድሮ ለ84ኛ ጊዜ በሚከበረው የአገው ፈረሰኞች በአል ላይ የሚሳተፉ ፈረሰኞች ቁጥር ከባለፉት አመታት ያነሰ ነው ተብሏል፡፡

በክልሉ ካለው አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ በዘንድሮ የአገው ፈረሰኞች በአል ላይ የሚወዳደሩ ፈረሰኞ ቁጥር ከ3ሺህ አይበልጥም ነው የተባለው፡፡

የአገው ፈረሰኞች ማኅበር ሊቀመንበር አለቃ ጥላዬ አየነው ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንደተናገሩት ለበአሉ አከባበር ዝግጅት አድርገን ጨርሰናል ብለው በውድድሩ የሚሳተፉ ተወዳዳሪዎች ለይተናል ብለዋል፡፡

ከ62ሺህ በላይ አባላት ያሉት የአገው ፈረሰኞች ማህበር ከ1930 አንስቶ በየአመቱ ቀኑን ለማስታወስ የፈረስ ጉግስ የፈረስ ሽምጥ እና ሌሎችም ጨዋታዎች እያካሄደ ይገኛል፡፡

በውድድሩ ከሚሳተፉ ተወዳዳሪዎች መካከል 12 የሚሆኑት ሴት ተወዳዳሪዎች መሆናቸው የተናገሩት አለቃ ጥላዬ የሚወዳደሩትም በፈረስ ሽምጥ ዘርፍ ነው ብለዋል፡፡

የአገው ፈረሰኞች በአል የህዝብ በአል እንጂ የፖለቲካ በአል አይደለም ያሉት ሊቀመንበሩ ከበአሉ አከባበር ጋር በተያያዘ ምንም የሚፈጠር የጸጥታ ስጋት የለብንም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የአገው ፈረሰኞች ማህበር የፍቅር ማሀበር ነው በክልሉ ያለው አለመረጋጋት በአከባበሩ ላይ የሚፈጥረው ችግር አይኖርም ብለዋል፡፡

የአገው ፈረሰኞች ማኅበር የአገው አባቶች ከሌሎች አባት አርበኞች ጋር በመተባበር የጣልያንን ወራሪ ጦር ዓድዋ ላይ ድል መቀዳጀታቸውን ለመዘከር በየዓመቱ ጥር 23 በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር የሚከበር በዓል ነው፡፡

ማኅበሩ በ1932 ዓ.ም ከ30 በማይበልጡ አባላት የተመሰረተ ሲሆን÷ በአሁኑ ወቅት ከ 62 ሺ በላይ አባላት ያሉት ሲሆን የአባላቱን ቁጥር 150 ሺ ለማድረስ ታቅዶ እየተሠራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የአገው ፈረሰኞች በአል በኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን በኩል የምዝገባ ሰርተፍኬት የተሰጠው ሲሆን በዩኔስኮ ለማስመስዘገብ አስፈላጊ መሰፈርቶች መሟላታቸው የተናገሩት አለቃ ጥላዬ በተያዘው 2016 አመት መጨረሻ ላይ ይመዘገባል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

የዘንድሮ የአገው ፈረሰኞች ማህበር በአል ጥር 23 ቀን 2016 አመት በአማራ ክልል አዊ ብሄረሰብ ዞን በአገው ምድር ኢንጂባራ ላይ የሚከበር ይሆናል፡፡

ሔኖክ ወ/ገበርኤል

ጥር 09 ቀን 2016 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply