በየመን ጀልባ ተገልብጦ 14 ሰዎች ሞቱ

https://gdb.voanews.com/01000000-0aff-0242-e4e6-08db1fe9cf1f_w800_h450.jpg

በየመን በኩል በሚገኘው የቀይ ባህር ዳርቻ አንድ ጀልባ ተገልብጦ ሕጻናትን ጨምሮ 14 የሚሆኑ ሰዎች መሞታቸውን የአሶስዬትድ ፕረስ ዜና ወኪል ከካይሮ ዘግቧል፡፡

ከሁለት ደርዘን በላይ ሰዎችን አሳፍሮ የነበረው ጀልባ ሲገለበጥ 11 ሴቶች እና 3 ሕጻናት ሲሞቱ፣ ሌሎች 11 ሰዎችና አንድ ሕጻን መትረፋቸውን ሆዲየዳ በተባለው ግዛት የሚገኝና በኢራን በሚደገፉት ሁቲ አማጺያን ሥር የሚተዳደር የዓሣ ምርት ባለሥልጣን አስታውቋል፡፡

ግለሰቦቹ ወደ ዘመድ ሠርግ በማምራት ላይ ሳሉ ንፋስና ወጀብ በመነሳቱ ጀልባቸው ሊገለበጥ መቻሉ ታውቋል፡፡ አስከሬኖችን እንዲፈልጉ ባለሥልጣናት የባህር ድንበር ጠባቂዎችን ወደ አካባቢው ልከዋል፡፡

ከዚህ በፊት እንዲህ አይነት አደጋ የሚገጥማቸው ከኢትዮጵያ፣ ጂቡቲ እና ሶማሊያ በመነሳት ወደ አረብ አገራት ለመሻገር የሚሞክሩ ፍልሰተኞች ነበሩ፡፡

ላለፉት አሥር ዓመታት በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የምትገኘው የመን በዓለም አከፊው የሰብዓዊ ቀውስ ያለባት አገር ስትሆን፣ አገሪቱ የረሃብ ጠርዝ ላይ ትገኛለች ተብሏል፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply