በደምቢዶሎ ተማሪዎችን አግተዋል በሚል የተጠረጠሩ ግለሰቦች ያቀረቡት የክስ መቃወሚያ ውድቅ ተደረገ

በደምቢዶሎ ተማሪዎችን አግተዋል በሚል የተጠረጠሩ ግለሰቦች ያቀረቡት የክስ መቃወሚያ ውድቅ ተደረገ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በደምቢዶሎ ተማሪዎችን አግተዋል በሚል የተጠረጠሩ 17 ግለሰቦች ያቀረቡት የክስ መቃወሚያ ውድቅ ተደረገ።

ዐቃቤ ህግ በእነ ከሊፋ አብዱረህማን በሚጠራው የክስ መዝገብ በ17 ግለሰቦች ላይ በህዳር 24 እና 25 ቀን 2012 ዓ.ም ከአማራ ክልል የሄዱ ተማሪዎችን በመለየት ማገታቸውን ጠቅሶ የፀረ ሽብርተኝነትን አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 3/3 በመተላለፍ እንደ ወንጀል ተሳትፏቸው ሶስት ክስ ማቅረቡ ይታወሳል።

ዛሬ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 1ኛ የህገ መንግስትና የፀረ ሽብር ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ከሊፋ አብዱረህማንን ጨምሮ ዘጠኝ ተከሳሾች ቀርበዋል።

ወደ ቤተሰብ እየተመለሱ የነበሩ የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን መታወቂያቸውን በመለየት ከተሳፈሩበት ተሽከርካሪ በማስወረድ አግተው አሳልፈው ለኦነግ ሸኔ በመስጠት እና በወቅቱ ተሽከርካሪ በማሽከርከር እንዲሁም በረዳትነት ሲሰሩና ለወንጀሉ በመተባበር መረጃውን ከፀጥታ አካል ደብቀዋል የተባሉ ግለሰቦች ላይ ሶስት ክስ ዐቃቤ ህግ ማቅረቡ የሚታወስ ነው።

ይሁን እና ይህ ክስ እንደ አጠቃላይ የሽብር አዋጁን ማቋቋሚያ ፍሬ ስለማያሟላና የተጠቀሰው አዋጅና ድንጋጌዎች ስለማይጣጣሙ 1ኛው ክስ ሙሉ በሙሉ ውድቅ ይደረግልን ሲሉ መቃወሚያ አቅርበው ነበር።

በዚህ መልኩም ዐቃቤ ህግ የኦነግ ሸኔ የፖለቲካ ወይም የርዮተ አለም አላማቸውን ለማራመድ ህዝብን ለማሸበር ወይም መንግስትን ለማስገደድ በማሰብ የወንጀል ድርጊት በሚሰጠው ውጤት ተካፋይ በመሆን እና የራሳቸው በማድረግ በቀጥታ በመፈጸም እና ወንጀሉን ለመፈጸም ቅድመ ዝግጅት በማድረግ በደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ወስጥ የተፈጠረውን የተማሪዎች ግጭት በመፍራት፤ ወደቤተሰቦቻቸው ሲያቀኑ የነበሩ የአማራ ከልል ተማሪዎችን ከተሳፈሩበት ተሽከርካሪ በማስወረድና መታወቂያቸውን በመለየት ከአማራ ክልል የመጡ መሆናቸውን በመለየት ተማሪዎቹን ማገታቸውን በመጥቀስ ይህም በፀረ ሽብር አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 3 የተመለከተውን የህጉን ፍሬ ነገር የሚያሟላ በመሆኑ በተከሳሾች የቀረበው መቃወሚያ ውድቅ ይደረግልኝ ሲል በጽሁፍ ምላሽ ሰጥቶ ነበር።

ፍርድ ቤቱም የተከሳሾቹን መቃወሚያ ውድቅ አድርጓል።

ሌላው በተከሳሾች በኩል ክሱ የቀረበው በተሻረ አዋጅ በመሆኑ ክሱ መቅረብ ያለበት በአዲሱ አዋጅ መሰረት ነው በሚል ላቀረቡት መቃወሚያ ዐቃቤ ህግ በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ህግ አንቀጽ 5 የወንጀል ህግ ወደ ኋላ ተመልሶ የማይሰራ በመሆኑ በሚደነገገው ንዑስ ቁጥር 1 ስር እንደተቀመጠው አዲሱ በተሻረው የወንጀል ህግ እንደ ወንጀል የተቆጠረ ድርጊት የተፈጸመው አዲሱ ህግ ከመጽናቱ በፊት በመሆኑ ጉዳዩ የሚታየው በተኛረው ህግ በመሆኑ ተከሳሾቹም ፈጽመውታል የተባለው የወንጀል ድርጊት ህዳር 22 ቀን 2012 ዓ.ም መሆኑን በመጥቀስ አዲሱ አዋጅ ቁጥር 1176/1012 ጸድቆ ስራ ላይ የዋለው መጋቢት 16 ቀን 2012 ዓ.ም መሆኑን በመጥቀስ ክሱ በተሻረው መቅረቡ ህግን የተከተለ ነው ሲል የተከሳሾቹ መቃወሚያ ውድቅ ተደርጓል።

በሌላ በኩል የዐቃቤ ህግ ምስክሮች ስም ዝርዝር ይገለጽልን ሲሉ ላቀረቡት መቃወሚያ ለደህንነታቸው ሲባል የስም ዝርዝራቸው መገለጽ የለበትም ሲል ያቀረበውን ምላሽ የመረመረው ችሎቱ ምስክሮች ደምቢዶሎ መኖራቸውን ተከትሎ ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው መገለጽ የለበትም ሲል ስማቸው እንዲገለጽ ያቀረቡትን መቃወሚያ ውድቅ አድርጓል።

በዚህ መሰረት የተከሳሾቹን የእምነት ክህደት ቃል ለመመልከት ፍርድ ቤቱ ለጥቅምት 25 ቀን 2013 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
የዐቃቤ ህግ የሰነድ ማስረጃም በዚህ ቀጠሮ ተተርጉሞ እንዲቀርብ አዟል።

በታሪክ አዱኛ

The post በደምቢዶሎ ተማሪዎችን አግተዋል በሚል የተጠረጠሩ ግለሰቦች ያቀረቡት የክስ መቃወሚያ ውድቅ ተደረገ appeared first on Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C.

Source: Link to the Post

Leave a Reply