በደራ ወረዳ ገብሮ በተባለ ቀበሌ ሽፍቶች በንፁሀን አማራዎች ላይ የሚፈፅሙት ግድያ እና ዝርፊያ ተጠናክሮ በመቀጠሉ መንግስት የመከላከያ ሰራዊት እንዲያስገባ ተጠየቀ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ…

በደራ ወረዳ ገብሮ በተባለ ቀበሌ ሽፍቶች በንፁሀን አማራዎች ላይ የሚፈፅሙት ግድያ እና ዝርፊያ ተጠናክሮ በመቀጠሉ መንግስት የመከላከያ ሰራዊት እንዲያስገባ ተጠየቀ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ጥቅምት 20 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ በኦሮሚያ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ ከኦነግ ሸኔ ጋር ግንኙነት አላቸው በሚባሉ ሽፍቶች በንፁሀን አማራዎች ላይ የሚፈፅሙት የግፍ ግድያ ተጠናክሮ መቀጠሉ እንዳሳሰባቸው በሸዋ የደራ አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ሰብሳቢ መ/ር ሀይለ ሚካኤል አርዓያ ተናግረዋል። የኦሮሚያ ክልል መንግስትም ሆነ የደራ መስተዳድር አካላት አማራን ከነፍሰ ገዳዮች እየታደጉ ባለመሆኑ የፌደራል መንግስት እጁን እንዲያስገባ ጠይቀዋል። መ/ር ሀይለ ሚካኤል እንደአብነት ሲጠቅሱም በደራ ወረዳ በቱቲ ዞን ገብሮ በተባለ ቀበሌ አመዳሚት ጎጥ ላይ ትናንት ጥቅምት 19 ቀን 2013 ዓ.ም ከቀኑ 5 ሰዓት ላይ አዝመራ እየጠበቁ የነበሩ አባትና ልጅ በጥይት ተገድለው መገኘታቸውንና ዛሬ ስርዓተ ቀብራቸው መፈፀሙን አስታውቀዋል። በተመሳሳይ ቀበሌ ከ15 ቀናት በፊትም ሁለት ወንድማማቾች፣አንድ የኦሮሚያ ልዩ ሀይል አባል ከታጣቂዎች በተተኮሰ ጥይት የተገደሉ ሲሆን የቆሰለ ሰው ስለመኖሩም ተናግረዋል። ታጣቂዎች የፀጥታ አካላትን ጭምር መንገድ ላይ ጠብቀው በመቆየት እየገደሏቸው መሆኑን ተናግረዋል። ከቀናት በፊትም በደራ ዋና ከተማ ጉንዶ መስቀል ከተማ ቀበሌ 2 አካባቢ ሳይቀር ሌሊት ላይ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች አንድን ሰው ከመኖሪያ ቤቱ በማስወጣት ገድለዋል። በደራ ወረዳ እገታ፣ግድያና ዝርፊያ በተደጋጋሚ እየተፈፀመ ነው ያሉት መ/ር ሀይለ ሚካኤል አንዳንድ የፀጥታ አካላትም መሬቱን እንጅ አማራን አንጠብቅም እንደሚሉ ጠቅሰው የፌደራል መንግስት ጣልቃ ገብቶ ማስተካከል አለበት ሲሉም አሳስበዋል። የፌደራል መንግስት ጣልቃ ገብቶ ህዝቡን የማይታደግ ከሆነ ግን የዘር ማጥፋት እንዲፈፀም የፈቀደ መሆኑን ማወቅ አለበት ብለዋል። የበሰሜን ሸዋ ዞን የደራ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ቦዳናን በስልክ ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት ፍቃደኛ ባለመሆናቸው አልተሳካም። ከቀናት በፊት ለደራ የተፈቀደ ደረጃውን የጠበቀ ከፍተኛ ት/ቤት መከልከሉም ከአማራ ማንነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ አካባቢው እንዳይለማ የሚፈልጉ አመራሮች ሆንብለው ያሳጠፉብን እድል ነው ሲሉ ቅሬታ ማቅረባቸውና የትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊው ማስተባበያ መስጠታቸው ይታወሳል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply