በደሴ ከተማ በሚያሽከረክረው ታክሲ ውስጥ ያገኘውን ገንዘብ ለባለቤቱ የመለሰው ወጣት የከተማዋ የወጣቶች የበጎ ተግባር አምባሳደር ሆኖ ተሰየመ

ማክሰኞ ነሐሴ 10 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ)በደሴ ከተማ በተለምዶ ሳማ መንደር በሚባለው አካባቢ ነዋሪ የሆነው ወጣት ኤርሚያስ ባየ፤ ነሐሴ 07 ቀን 2014 በሚያሽከረክረው ታክሲ ውስጥ ወድቆ ያገኘውን የአስራ ስድስት ሺሕ ብር ለባለቤቱ በታማኝነት በማስረከቡ የከተማዋ የወጣቶች የበጎ ተግባር አምባሳደር ተደርጎ ተሰይሟል።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ም/ከንቲባ ሱለይማን እሸቱ ወጣት ኤርሚያስ ባየ ባደረገው በጎ ተግባር ከተማ አስተዳደሩ የከተማዋ የወጣቶች የበጎ ተግባር አምባሳደር አድርጎ በመሠየም፤ ለተግባሩ እውቅናና የ10 ሺሕ ብር ገንዘብ ስጦታ እንዳበረከተለት ገልጸው፤ ከከተማ አስተዳደሩ ጋርም የበጎ ተግባር ሥራውን አብሮ እንዲሠራም እናደርጋለን ብለዋል።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ሀላፊ ኮማንደር አሳምነው ሙላት በዚህ የኑሮ ውድነትና ታክሲዎች የተሳፋሪን መልስ በአግባቡ ለመስጠት ባልቻሉበት ወቅት፤ ኹሉን ተቋቁሞ ገንዘባቸውን ታክሲ ውስጥ ለጣሉት እናት መመለሡ የኛም አምባሳደር ነውና ለሌሎችም የታክሲነ ባጃ አሽከርካዎች አስተማሪያችን በመሆኑ እውቅና ሰጥተናል ብለዋል።

ወጣት ኤርሚያስ ባዩ በታክሲና ባጃጅ ላይ ዕቃ ወድቆ አይሰጡም የሚለውን አስተሳሰብ ህዝቡ አስወግዶ፤ ዕቃ ሲጠፋቸው ለባለ ታክሲዎችና ባለ ባጃጆች ባለንብረት ማህበር ወዲያውኑ ቢያሳውቁ ብዙ ቅን የሆኑ ሾፌሮችና ረዳቶች ስላሉ የጠፋባቸውን ንብረት ማግኘት እንደሚችሉ ገልጿል።

የተደረገለትን የገንዘብ ስጦታና የእውቅና ምሥክር ወረቀት አመስግኖም፤ በጎ መሥራት ጥቅሙ ለራሳችን ስለሆነ የከተማችን ወጣቶችም የደሴ መገለጫ የሆነውን በጎ ተግባር ይበልጥ አጠናክረው እንዲቀጥሉ መልእክቱን ማስተላለፉን ከከተማ አስተዳደሩ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።

ከደሴ ከተማ አስተዳደር በተጨማሪም በከተማዋ ፖሊስ መምሪያ እና በቅርብ ጉደኞቹ የእውቅና ምስክር ወረቀትና የገንዘብ ስጦታም ለወጣት ኤርሚያስ ባየ እንደተበረከተለት ተገልጿል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply