በደቡብ ኢትዮጵያ ሰገን ዞን በአማሮ ልዩ ወረዳ በአማሮች ላይ፣በኮንሶ ዞን ከጉማይዴ በተወሰዱ ቀበሌዎች ደግሞ በተለያዩ የህ/ሰብ ክፍሎች ላይ አነጣጥሮ በጦር መሳሪያ በመታገዝ ጭምር ተፈፅሟል…

በደቡብ ኢትዮጵያ ሰገን ዞን በአማሮ ልዩ ወረዳ በአማሮች ላይ፣በኮንሶ ዞን ከጉማይዴ በተወሰዱ ቀበሌዎች ደግሞ በተለያዩ የህ/ሰብ ክፍሎች ላይ አነጣጥሮ በጦር መሳሪያ በመታገዝ ጭምር ተፈፅሟል በተባለው ጥቃት በርካቶች ሲገደሉና ሲቆስሉ ሽህዎች ተፈናቀሉ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ህዳር 12 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ በደቡብ ኢትዮጵያ በሰገን ዞን በአማሮ ልዩ ወረዳ ቡኒቲ አካባቢ ከህዳር 5 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በአማራዎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ተፈፅሟል። ከህዳር 5 እስከ ህዳር 9 ቀን 2013 ዓ.ም በመንግስት አካላት ጭምር በመታገዝ በንፁሀን ላይ ተፈፅሟል በተባለው በጦር መሳሪያ የታገዘ ጥቃት በርካታ አማራዎች ተገድለዋል፤ ቆስለዋል፤ ታፍነዋል፣ ሽህዎች ወደ አርባ ምንጭና ወደ ሌሎች አካቢዎች ተፈናቅለዋል። የበርካታ ቀበሌ ነዋሪዎች ሀብት ንብረታቸው ተዘርፏል፣ የመኖሪያ ቤታቸው ሙሉ በሙሉ በሚባል አግባብ ወድሟል። የቀድሞው የቡኒቲ ቀበሌ ሊቀመንበር አቶ ባይናክ በዙ ከአሁን ቀደም በአማራ ላይ በተፈፀመው ጥቃት በዋና አድራጊነት ወንጀል ተጠርጥረው የተከሰሱ ቢሆንም የወረዳ አመራሮች በአካባቢው የለም በሚል አሳልፈው ባለመስጠታቸው እየተከሰተ ያለ ማንነት ተኮር ጥቃት ስለመሆኑም ተገልጧል። አቶ ባይናክ በዙ የተባሉት ተጠርጣሪ በአንድ ወቅት “ፌስታልህን ጠቅልለህ መውጣት ትችላለህ!” በማለት ግጭት ቀስቃሽና ከአንድ አመራር የማይጠበቅ ንግግር ማድረጋቸውና ይህን ተከትሎም በቡኒቲ አማራዎች ላይ ግድያና ማፈናቀል መከሰቱ ይታወሳል። ከሰሞኑም 15 የሚሆኑ በህወሀት የገንዘብና የስልጠና ድጋፍ የሚደረገላቸው በድብቅ እስከ መቀሌ ድረስ የሄዱ በሚል በኮንሶ ዞን በ4 ከተሞች መታሰራቸውን ነዋሪዎች አውስተዋል። ጉማይዴ የሚባል ብሄር የለም የሚሉ የክልልና የዞን አመራሮችም የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች የሚኖሩበትን ጉማይዴን ለኮንሶ ዞን 9 ፣ለአማሮ 3፣ ለቡርዥ 4፣ ለደራሼ 1 ቀበሌዎችን ያለህዝቡ ይሁንታ ያከፋፈሉ ስለመሆናቸው ነዋሪዎች ገልፀዋል። በ2011 ዓ.ም ኮንሶ በዞን ሲደራጅ አሌና ቡርዥ ልዩ ወረዳ ተቀብለዋል፤ አማሮና ደራሼ ልዩ ወረዳዎች በወረቀት እንጅ ልዩ ወረዳው እንኳ በተግባር አልተፈፀመላቸውም ተብሏል። ጉማይዴም ራሴን ችዬ በዞን መደራጀት አለብኝ እንጅ ተበታትኜ ህልውናዬን ማጣት የለብኝም፣ አማሮም ከልዩ ወረዳ ወደ ልዩ ወረዳ ሳይሆን ወደ ዞን ማደግ አለብኝ የሚሉ ጥያቄዎች አንስተው በመጠየቃቸው ከክልል እስከ ዞንና ወረዳ ድረስ ባሉ በጥያቄው ባልተደሰቱ አመራሮችና የፀጥታ አካላት ከባድስቃይ፣አፈና፣እስር፣እንግልት፣መፈናቀል ደርሶብናል፤ በርካታ ሴቶች እና ህጻናትም ተደፍረዋል ብለዋል። የጉማይዴና የአማሮ ነዋሪዎች ላለፉት 3 ዓመታት በመንገድ፣በገበያ፣በውሀና መሰል የመሰረተ ልማቶች ሆንተብሎ እንዲጎዱ በማድረግ እየተቀጡ ነው፤ ታስረው ፍ/ቤት የፈታቸው እንኳ ለወራት በፖሊስ ተይዘው ያልተለቀቁና የተንኮላሹ፣ በፀጥታ አካላት የተደፈሩና ፍትህ ያላገኙ ሴቶች አሉ ሲሉም አክለዋል። በኮንሶ በኩል እየተፈፀመ ያለው በተኩስ የታገዘ ጥቃት ከህዳር 4 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ የቀጠለና በተለይም በደራሼንና በአሌም ብሄረሰብ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ ስለመሆኑ ምንጮች ተናግረዋል። ኦነግ ሸኔን ጭምር በያቤሎ በኩል አስገብተው በንፁሀን ላይ ጭፍጨፋ እየፈፀሙ መሆናቸውን ከአልባሳትና ከመታወቂያ መረጃዎች ለማረጋገጥ ስለመቻላቸው ነው ምንጮች የገለፁት። እንደ ቅሬታ አቅራቢዎች ሀሳብ ሙሉ በሙሉ ለም በሆነው በጉማይዴ የሚኖረውን አማራን ጨምሮ ሌሎች ህዝቦችን በማፈናቀል የራሴ የሚሉትን ህዝብ ለማስፈር ሆነብለው አልመው የሚሰሩ የኮንሶ ዞን አመራሮችና የፀጥታ አካላት ስላሉ መንግስት የመከላከያ ሰራዊት አስገብቶ የህዝቡን ሰላምና ደህንነት እንዲያስከብር ጠይቀዋል። የዞንና የአካባቢው የመስተዳድር አካላት አያሌ ንፁሀን ከተገደሉ፣ከተፈናቀሉና ሀብት ንብረት ከወደመ ከቀናት በኋላ ከህዳር 10 ጀምሮ ጥቃት ወደተፈፀመባቸው አካባቢዎች ማቅናታቸው ተገልጧል፤ አድራሻቸውን እንዳገኘን ምላሻቸውን አካተን የምንመለስ ይሆናል። ከአማሮ ወረዳ ነዋሪ ጋር የተደረገው ቆይታ በአማራ ሚዲያ ማዕከል/AMC የዩቱብ አድራሻ ስለተለቀቀ መከታተል ይችላሉ።

Source: Link to the Post

Leave a Reply