በደቡብ ክልል ለሀገር የመከላከያ ሰራዊት ከ153 ሚሊየን በላይ ብር ድጋፍ ማሰባሰብ መቻሉ ተገለፀ

በደቡብ ክልል ለሀገር የመከላከያ ሰራዊት ከ153 ሚሊየን በላይ ብር ድጋፍ ማሰባሰብ መቻሉ ተገለፀ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 14 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በደቡብ ክልል ለሀገር የመከላከያ ሰራዊት ከ153 ሚሊየን በላይ ብር ድጋፍ ማሰባሰብ እንደተቻለ ተገለፀ።

የደቡብ ክልል ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ እና የመከላከያ ሰራዊት ሀብት አሰባሰብ ግብረ ሀይል ሰብሳቢ አቶ ተፈሪ አባተ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ በሰጡት መግለጫ፥ ጽንፈኛው የህወሓት ቡድን በመከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመው ክህደት በክልሉ ህዝብ ላይ ቁጭት እና እልህ እንዲፈጠር በማድረጉ በአይነት እና በጥሬ ገንዘብ ከ153 ሚሊየን በላይ ሀብት ድጋፍ ማድረግ ተችሏል።

እንደ ኃላፊው ገለጻ የክልሉን ህዝብ በማስተባበር ባለፉት 7 ቀናት ብቻ ለጀግናው የመከላከያ ሰራዊት 1 ሺህ 586 ሰንጋዎች፣ 286 በግ እንዲሁም 430 የፍየል ርክክብ መደረጉን አስረድተዋል።

ኃላፊው አክለው እንደጠቆሙት 551 ኩንታል ጤፍ፣ ቅቤ፣ ማር እና መሰል መሠረታዊ ፍጆታዎችንም ህብረተሰቡ ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።

የመንግሥት ሰራተኞች ከወር ደመወዛቸው ድጋፍ ማድረጋቸውን የተናገሩት አቶ ተፈሪ፥ ከከፍተኛ አመራሩ ጀምሮ በየደረጃ ያለው ህብረተሰብ ከምንም በላይ ታላቅ ስጦታ የሆነውን ደም በመለገስ ለመከላከያ ሰራዊት አጋርነቱን በመግለጽ ላይ መሆኑንም ተናግረዋል።

በክልሉ 1 ቢሊየን ብር ድጋፍ ለማድረግ መታቀዱን ሀላፊው ጠቁመው አሁን እየተደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አብራርተዋል።

እንደ ሀላፊው ገለጻ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሂሳብ ቁጥር 1000354443892  በመክፈት ለመከላከያ ሰራዊቱ ድጋፍ የማድረጉ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ከክልሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

The post በደቡብ ክልል ለሀገር የመከላከያ ሰራዊት ከ153 ሚሊየን በላይ ብር ድጋፍ ማሰባሰብ መቻሉ ተገለፀ appeared first on Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C.

Source: Link to the Post

Leave a Reply