ሐሙስ የካቲት 9 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ኅብረት ለምርጫ በደቡብ ብ/ብ/ሕ ክልል በሚገኙ ስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች ጥር 29/2015 በተደረገው ሕዝበ-ውሳኔ ላይ ባወጣው የመጀመሪያ ደረጃ የትዝብት ሪፖርት በምርመራ ያረጋገጣቸውን 24 አሳሳቢ ኹነቶች ይፋ አድርጓል፡፡
434 ቋሚና 76 ተንቀሳቃሽ ታዛቢዎችን በአባል ድርጅቶቹ በኩል በማሰማራት ሕዝበ ውሳኔውን የታዘበው ኅብረት ለምርጫ፣ በታዛቢዎች ከባድ የሆኑ እንዲሁም በሕዝበ ውሳኔው ሂደት እና ውጤት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ 104 አሳሳቢ ኹነቶች ሪፖርት እንደተደረጉለት ያስታወቀ ሲሆን፣ ከነዚህ ሁነቶች መካከል የተጣሩ እና የተረጋገጡ 24 አሳሳቢ ኹነቶችን በትዝብት ሪፖርቱ አካቷል፡፡
በሪፖርቱ ይፋ ከተደረጉ ኹነቶች መካከል በተከለከሉ 3 ቦታዎች ላይ የምርጫ ጣቢያዎች መቋቋም፣ በ6 የምርጫ ጣቢያዎች ያልተፈቀደላቸው ግለሰቦች መገኘት፣ በተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች ከ70 በላይ በመራጮች መዝገብ ላይ ሥማቸው ያልተመዘገቡ ሰዎች ድምጽ መስጠት እንዲሁም በምርጫ አስፈጻሚዎች የድምጽ መስጠት ሂደት ምስጢራዊነት መጣስ ይገኙበታል፡፡
በተጨማሪም፤ በጌዴኦ ዞን ገደብ ወረዳ በሚገኝ አንድ የምርጫ ጣቢያ የድምፅ ቆጠራ በሚካሄድበት ወቅት የወረዳው አስተዳደር ባለስልጣናት በምርጫ ጣቢያው ተገኝተው ነበር የተባለ ሲሆን፣ በጎፋ ዞን ሳውላ ከተማ በሚገኝ አንድ የምርጫ ጣቢያ ደግሞ የብልፅግና ፓርቲ አባላት በድምፅ መስጠት ወቅት በጣቢያው ተገኝተው እንደነበር ተነግሯል፡፡
ኅብረት ለምርጫ እነዚህ ሕገወጥ ድርጊቶች እና ጥሰቶች አግባብነት ባለው አካል ክትትል እና ምርመራ እንደሚደረግባቸው ተስፋ አደርጋለሁ ያለ ሲሆን፣ በአጥፊዎች ላይ የሚጣለው ቅጣት ተመሳሳይ ችግሮች እንዳይከሰቱ የሚያስተምር መሆን አለበት ብሏል፡፡
በአጠቃላይ ሕዝበ ውሳኔው ምርጫ ቦርድ ከዚህ በፊት ከነበረው አፈጻጸም አኳያ የድምጽ መስጫ ቁሳቁሶችን በማቅረብ ረገድ ከፍተኛ መሻሻል ያሳየበት እንደሆነ ያስታወቀው ኅብረት ለምርጫ፣ በአሳሳቢ ኹነቶች ላይ ከሚወሰዱ እርምጃዎች ባሻገር መሻሻል ያለባቸውን ጉዳዮች ይፋ አድርጓል፡፡
ኅብረት ለምርጫ ከሕዝበ ውሳኔው የድምፅ መስጫ ዕለት በኋላ ያለውን ድህረ ሕዝበ ውሳኔ ከባቢን 50 ታዛቢዎችን አሰማርቶ እየተከታተለ መሆኑን ያስታወቀ ሲሆን፣ በቀጣይ የሕዝበ ውሳኔ እና የድህረ-ህዝበ ውሳኔ ግኝቶችን እንዲሁም የውሳኔ ሃሳቦችን ጨምሮ አጠቃላይ የትዝብት ሪፖርት በማዘጋጀት ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥር 29/2015 የተካሄደውን የሕዝበ ውሣኔ የመጨረሻውን ውጤት የማጣራትና የማረጋገጥ ሥራ የካቲት 6/2015 አርባ ምንጭ ከተማ በሚገኘው የሕዝበ ውሣኔው ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት መጀመሩን አስታውቋል።
ይህንም ተከትሎ በማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቱ የተጣራውንና በቦርዱ የተረጋገጠውን የመጨረሻው የሕዝበ ውሣኔ ውጤት ትናንት የካቲት 8/2015 ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረግ ያስታወቀ ቢሆንም እስከአሁን ግን ውጤቱ ይፋ አልተደረገም።
The post በደቡብ ክልል በተካሄደው ሕዝበ ውሳኔ ላይ 24 አሳሳቢ የሕግ ጥሰቶች መገኘታቸው ተገለጸ first appeared on Addis Maleda.
Source: Link to the Post