በደቡብ ክልል ተፎካካሪ ፓርቲን የመረጡ የቁጫ ማኅበረሰብ አባላት መገለል እየደረሰባቸው ነው ተባለ

ዕረቡ ሐምሌ 20 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ተፎካካሪ ፓርቲዎችን መርጣችኋል ተብለው የአካባቢው ማኅበረሰብ አባላት ከእርሻ፣ ከንግድ፣ ከትምህርት እና ከመንግሥት ሥራ በይፋ ተሰናብተዋል፤ መገለልም እየደረሰባቸው ነው ሲል የቁጫ ምርጫ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስታወቀ፡፡

የቁጫ ምርጫ ክልል ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በመቶ የሚቆጠሩ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችን የመረጡና አባል የሆኑ ሰዎች በመንግሥት መታሰራቸውን ገልጿል፡፡ በእስር ላይ የሚገኙ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አባላት በፖሊስ ድብደባ እየተፈጸመባቸው መሆኑንም ምክር ቤቱ ጠቁሟል፡፡

የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አባላት ተገደው የብልጽግና ፓርቲ አባል እንዲሆኑ ጥይት ተደግግኖባቸው፤ የብልጽግና ፓርቲ አባልት ፎርም እንዲሞሉ መገደዳቸውንም ምክር ቤቱ በመግለጫው አብራርቷል፡፡

በቁጫ ምርጫ ክልል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወዳድረው አሸናፊ ሆነው ማኅበረሰቡን የወከሉ ሰዎች፤ ከወከላቸው ማኅበረሰብ ጋር እንዳይወያዩ፣ በፖሊስ ታግተውና ማስፈራሪያ ደርሶባቸው ተመልሰዋል ተብሏል፡፡

በመንግሥት ላይ አቤቱታ ያቀረቡት ፓርቲዎች የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቁሕዴፓ)፣ የኢትዮጵያ ሕዝን ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) እና የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ናቸው፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply