በደቡብ ክልል የሚገኙ 10 ዞኖችና 6 ልዩ ወረዳዎች በክልል የመደራጀት ጥያቄ ለፌደሬሽን ምክር ቤት አቀረቡ

ሐሙስ ሐምሌ 28 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል የመገኙ 10 ዞኖችና 6 ልዩ ወረዳዎች በክልል የመደራጀት ጥያቄን በዛሬው ዕለት ለፌደሬሽን ምክር ቤት አቅርበዋል።

የደቡብ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ክፍሌ ዋና ሰሞኑን በክልል የመደራጀት ጥያቄ ያቀረቡ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች በኹለት ክልል ለመደራጀት ያቀረቡትን ጥያቄ ሰነድ ለፌደሬሽን ምክርቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር አስረክበዋል።

የሚደራጁት ክልሎች የህዝቦችን አንድነት እንዲሁም የጋራ እሴቶችን በሚያጎላ እና መልኩ ሊሆን እንደሚገባ በምክርቤቶቻቸው የጋራ አቋም መያዛቸውን ገልጸዋል።

በዚህም መሰረትወላይታ፣ጋሞ፣ጎፋ፣ኮንሶ፣ደቡብ ኦሞ፣ጌዴኦ ዞኖች፣እንዲሁም ደራሼ፣ባስኬቶ፣ኸሌ፣አማሮ እና ቡርጂ ልዩ ወረዳዎች አንድ ላይ በክልል እንደራጃለን በማለት በየምክር ቤቶቻቸው በማጽደቅ መወሰናቸውን ምክትል አፈ ጉባኤው ገልጸዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ስልጤ ፣ከምባታ ጠምባሮ፣ሀዲያ ፣ሀላባ፣የም ልዩ ወረዳ በአንድ ላይ በመሆን ክልል ለመመስረት በምክር ቤቶቻቸው በማጽደቅ የጋራ አቋም መያዛቸውንም ጠቁመዋል።

የፌደሬሽን ምክር ቤት በህገ መንግስቱ የተሰጠውን ስልጣን መሰረት በማድረግ በሚወስነው ውሳኔ መሰረት ክልል ለመሆን መወሰናቸውን መግለጻቸውን የክልሉ ኮምዩኒኬሽን ቢሮ አስታውቋል።

የፌደሬሽን ምክርቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር እንደገለጹት፤ ኹሉም ምክር ቤቶች ያስተላለፉት ውሳኔ የህዝቦችን ውክልና ያሳየ መሆኑን አብራርተዋል።

በዚህም መሰረት 10 ዞንኖች እና 6 ልዩ ወረዳዎች በኹለት ክልል ለመደራጀት ያቀረቡትን ጥያቄ ምክር ቤቱ መቀበሉን አረጋግጠዋል።

በመርሐ ግብሩ ከ10 ዞኖችና ከ6 ልዩ ወረዳዎች የተውጣጡ የምክር ቤት አፈ ጉባኤዎች መገኘታቸውም ታውቋል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply