
በደቡብ ወሎ ዞን አርጎባ ከመጠለያ ውጭ ያሉ ተፈናቃዮች ለከፍተኛ ችግር መዳረጋቸውን ገለጹ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ የካቲት 16 ቀን 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ሸዋ በደቡብ ወሎ ዞን አርጎባ መጠለያ ሞልቷል በመባሉ ውጭ ላይ ሆነው በየዘመዱ ተጠግተው የሚኖሩ ተፈናቃዮች ለከፍተኛ ችግር መዳረጋቸውን ገልጸዋል። ተፈናቃዮች ባሉበት የተመዘገቡ እና እርዳታም ከሁለት ወር በፊት ለእያንዳንዱ ግለሰብ 15 ኪሎ ግራም ስንዴ የተሰጣቸው መሆኑ ታውቋል። ቅሬታ አቅራቢዎቹ ሰኔ 11/2014 በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ በአሸባሪ እና ወራሪ ኦነጋዊያን ከተፈጸመው አማራ ተኮር ጭፍጨፋ የተረፉ ናቸው። ችግራቸው ይፈታ ዘንድም አምስት የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትን በመወከል እየተንቀሳቀሱ ቢሆንም እስካሁን እዚህ ግባ የሚባል የሰብአዊ እርዳታ እየደረሰን አይደለም ብለዋል። ከሞላ ጎደል የህክምና ክትትል እና ድጋፍ እያገኙ መሆኑን ተናግረዋል። አሁንም የሰብአዊነት ጉዳይ ይገደኛል የሚል ሁሉ መጠለያ እና እርዳታ በማቅረቡ ረገድ ከጎናቸው እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።
Source: Link to the Post