በደብረ ብርሃን-አዲስ አበባ መስመር የተፈጠረዉ ችግር ምንድን ነዉ?ከደብረ ብርሃን አዲስ አበባ መስመር በዛሬዉ ዕለት የትራንስፖርት አገልግሎት መቋረጡን ኢትዮ ኤፍ ኤም ከደብረ ብርሃን ከ…

በደብረ ብርሃን-አዲስ አበባ መስመር የተፈጠረዉ ችግር ምንድን ነዉ?

ከደብረ ብርሃን አዲስ አበባ መስመር በዛሬዉ ዕለት የትራንስፖርት አገልግሎት መቋረጡን ኢትዮ ኤፍ ኤም ከደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪዎችና ከዞኑ ትረንስፖርት ኃላፊዎች ማረጋገጥ ችሏል፡፡

የሰሜን ሸዋ ዞን የትራንስፖርት ማህበራት ጥምረት ሰብሳቢ አቶ ገብረ እግዚአብሄር ተሰማ ከኢትዮ ኤፍ ኤም ጋር በነበራቸዉ ቆይታ፣ ከደብረ ብርሃን አዲስ አበባ የሚመላለሱ አሸከርካሪዎች ሰንዳፋ ከተማ ላይ አላግባብ እየተከሰሱ በመሆናቸዉ መስራት አልቻሉም ብለዋል፡፡

የታርጋ ቁጥራቸዉ አማራ በሆኑ ተሸከርካሪዎች ላይ ያለምንም ምክንያት የሰንዳፋና አካባቢዉ ትራፊክ ፖሊሶች እና የመንገድ ደህንነቶች ባለፉት ሁለት ተከታታይ ቀናት ያለማቋረጥ መክሰሳቸዉን አቶ ገብረ እግዚአብሄር አስታዉቀዋል፡፡

አሽከርካሪዎቹ ከ1 ሺህ 5 መቶ እስከ 2 ሺህ 5 መቶ ብር የሚደርስ ቅጣት እንደሚተላለፍባቸዉ ያነሱት ሰብሳቢዉ በዘህም ምክንያት መስራት እንዳልቻሉ ነግረዉናል፡፡

የትራፊክ ፖሊሶቹ ከክሱ በተጨማሪም አሽርካሪዎቹ ደግመዉ በዚያ መስመር እንዳይመጡ ማስፈራራታቸዉንም ኃላፊዉ ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ሁለት ቀናት ዉስጥ የታርጋ ቁጥራቸዉ አማራ የሚል ከ40 በላይ ተሸከርካሪዎች ያላግባብ እንደተከሰሱም ሰምተናል፡፡
እነዚህ አሽርካሪዎች ያለ ምክንያት መከሰሳቸዉን በምን አረጋገጣችሁ ብለን ለአቶ ገብረእግዚአብሔር ላነሳንላቸዉ ጥያቄም “ በደብረ ብርሃን መናኸሪያና መዉጫ ኬላዎች ላይ የትርፍና የታሪፍ ቁጥጥር እናደርጋለን” ብለዋል፡፡
ኢትዮ ኤፍ ኤም አሽከርካሪዎችን በጉዳዩ ላይ አናግሯል፡፡

አሽከርካሪዎቹም ከክሱ ባለፈም ስድብና ማስፈራሪያ እንደሚደርስባቸዉ ነግረዉናል፡፡
በዚህም የተነሳ ከፍተኛ ስጋት ዉስጥ ስለገባን የትራንስፖርት አገልግሎቱን መስጠት አልቻልንም ሲሉ ቅሬታቸዉን አሰምተዋል፡፡

የሰሜን ሸዋ ዞን የትራንስፖርት ማህበራት ጥምረት ሰብሳቢ አቶ ገብረ እግዚአብሄር ተሰማ ይህ ችግር ባለበት ሁኔታ ተሽከርካሪዎቹን ማሰማራት ባለመቻላችን መብታችን እስኪከበር አገልግሎቱን አቁመናል ብለዉናል፡፡

በአሽከርካሪዎች ላይ ከሚደርሰዉ ክስ በተጨማሪም የህዝብ ማመላለሻ ተሸርካሪዎች ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ ከሰንዳፋ፤ ከለገጣፎ ጭምር እንዲመለሱ መደረጉንም ሰብሳቢዉ አስታዉቀዋል፡፡

የትራንስፖርት አገልግሎቱን ያቋረጥነዉ አድማ ለመምታት ሳይሆን መብታችን እንዲከበር ነዉ ያሉት የማህበሩ ሰብሳቢ፣ የሚመለከታቸዉ አካላት አስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጠን ሲሉም ጠይቀዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጡን የሰሜን ሸዋ ዞን ትራንስፖርር መምሪያ ኃላፊ አቶ ሲሳይ ወልደ አማኑኤልን ብንጠይቅም ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡
ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ያለዉ መረጃ ይህ ነዉ፡፡

በአባቱ መረቀ
ሐማሌ 04 ቀን 2014 ዓ.ም

Source: Link to the Post

Leave a Reply