
በድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች ላይ በተወረወረ ድንጋይ ጉዳት መድረሱ ተገለጸ፤ በርካታ ተማሪዎች በግቢው ውስጥ ጨለማን ተገን አድርገው ከተደበቁ አካላት በተወረወረ ድንጋይ ጉዳት ስለደረሰባቸው ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል ተብሏል። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ጥር 30 ቀን 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ሸዋ በድሬድዋ ዩኒቨርስቲ በርካታ የሚሆኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች ጥር 29/2015 ከግቢ ወጥተው ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ እና በቅዱስ ሲኖዶስ ትዕዛዝ መሰረት ጥቁር በመልበስ የነነዌ ጾመ ምህላን በሰላም ሲያከናውኑ ውለው እንደነበር ለአማራ ሚዲያ ማዕከል (አሚማ) ገልጸዋል። ይሁን እንጅ ከቤተ ክርስቲያን በጾም እና በጸሎት ውለው ከቀኑ 12 ሰዓት ገደማ ወደ ድሬድዋ ዩኒቨርስቲ ግቢ እየገቡ በነበሩ ተማሪዎች ላይ ትንኮሳ መደረጉን ተከትሎ መሯሯጥ እንደነበር እንዲሁም በነበረው መገፋፋትም ወድቀው የተረጋገጡ ተማሪዎች ስለመኖራቸው ተገልጧል። ከምሽቱ 2 ሰዓት ገደማ ግን በአንደኛው የዩኒቨርስቲ መግቢያ በር እና በኤፍ ብሎክ አካባቢ ጨለማን ተገን አድርገው የተደበቁ አካላት ድንጋይ በመወርወር ጥቁር በለበሱ ምዕመናን ላይ ጉዳት አድርሰዋል ተብሏል። በዚህም ከግቢ የዐይን እማኞች እንደሚሉት ከ10 ያላነሱ የተዋህዶ ልጆች ተፈንክቶ መድማት እና መቁሰል ጉዳት ስላጋጠማቸው ከግቢ እንዲወጡ ተደርጎ ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል። በተወረወረ ድንጋይ የብሎክ መስታወት የተሰባበረባቸው አካባቢዎች እንዳሉም ተገልጧል። ተማሪዎቹ ለደህንነታቸው እንደሚሰጉ በመግለጽ የግቢው ጥበቃ እንዲጠናከርላቸው ጥሪ አድርገዋል። አማራ ሚዲያ ማዕከል (አሚማ) ጉዳዩን ለማጣራት እንዲሁም በተማሪዎች የደህንነት ስጋት እና ቅሬታ ላይ ምላሽ እንዲሰጡ በሚል ለድሬድዋ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ለዶ/ር ኡባህ አደም የእጅ ስልክ ላይ ደጋግሞ የደወለ ቢሆንም የሚጠራ ስልካቸውን ባለማንሳታቸው ለጊዜው ሀሳባቸውን ለማካተት አልቻለም። በድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ የተማሪዎች ህብረት ፕሬዝዳንት መሆኗን የገለጸችው ሜሮን “አልተዋወቅንም” በሚል ሰበብ በጉዳዩ ላይ አስተያዬት ከመስጠት ተቆጥባለች።
Source: Link to the Post