
በድሬድዋ ዩኒቨርስቲ የአማራ ተማሪዎችን ማሰር እና ማሳደዱ ተጠናክሮ እንደቀጠለ ነው፤ ከርሃብ አድማው ጋር በተያያዘ ዛሬ የታሰሩትን 8 ተማሪዎች ጨምሮ 14 አማራዎች በእስር ላይ ይገኛሉ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ የካቲት 30 ቀን 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ሸዋ በድሬድዋ ዩኒቨርስቲ የአማራ ተማሪዎችን ማሰር እና ማሳደዱ ተጠናክሮ እንደቀጠለ ነው፤ ከርሃብ አድማው ጋር በተያያዘ ዛሬ የታሰሩትን 8 ተማሪዎች ጨምሮ 14 አማራዎች የታሰሩ መሆኑን ከስፍራው ያሉ እና ድርጊቱን ያወገዙ ተማሪዎች አረጋግጠዋል። የካቲት 26/2015 ምሽት ከቤተ ክርስቲያን ወደ ድሬድዋ ዩኒቨርስቲ ግቢ እየገቡ ሳለ በተደራጁ የኦነግ ተልዕኮ አስፈጻሚ አካላት በድንጋይ ጥቃት የተፈጸመባቸው መሆኑን ተከትሎ ራሳቸውን በመከላከል እና በመሸሸ ላይ ከነበሩት መካከል 6 የአማራ ልጆች ተይዘው በሳቢያ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው ይገኛሉ። እነዚህም ለመጋቢት 7/2015 ተለዋጭ ቀጠሮ የተሰጣቸው መሆኑን አሚማ በቀደመ ዘገባው መዘገቡ ይታወሳል። የዩኒቨርስቲውን አካሄድ ያወገዙ ተማሪዎች በተናጠል እየሄዱ የታሰሩ ንጹሃን ይፈቱልን በሚል ቅሬታ ሲያቀርቡ ተሰሚነት ባለማግኘታቸው፣ ይባስ ብሎ እየታሰሩ መሆኑን ተከትሎ የካቲት 28/2015 የርሃብ አድማ አድርገዋል። ካፌ ውስጥ ገብተው ምሳ ባለመብላት ተቃውሟቸውን ማሰማታቸውን ተከትሎ የካቲት 30/2015 ዩኒቨርስቲው ስብሰባ አካሂዷል። የካቲት 30/2015 ከጠዋቱ 2 ሰዓት እስከ 6 ሰዓት ድረስ የድሬድዋ ዩኒቨርስቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር መገርሳ ሲሆኑ በተቀረጸው ቪዲዮ ላይ ታይታችኋል በሚል ወደ ካፌ ሲገቡ የተያዘው ከ400 በላይ ስም ዝርዝር በማስታወቂያ ቦርድ በመለጠፍ አስቸኳይ ስብሰባ አካሂደዋል። በስብሰባውም “የተቆራረጠ ቪዲዮ” በእስክሪን በማሳዬት ተማሪዎችን ተጠያቂ ናችሁ፤ እስከማባረር ድረስ እርምጃ እንወስዳለን ከማለታቸው ባሻገር የተማሪዎችን ሀሳብ አልተቀበሉም ተብሏል። ከአዳራሽ ከመውጣታቸውም የካቲት 29/2015 አስረው ወስደው አመሻሹን የለቀቋቸውን 3 ተማሪዎች ጨምሮ በድምሩ እንደ አዲስ 8 የአማራ ልጆችን ማሳሰራቸው ተገልጧል። በአጠቃላይ አሁን ላይ 14 የአማራ ተማሪዎች በግፍ እስር ላይ እንደሚገኙ ምንጮች ለአሚማ ተናግረዋል። ተማሪዎቹ አሁንም ትምህርት ሚኒስትርን ጨምሮ የሚመለከተው አካል በአስቸኳይ እጁን አስገብቶ ችግሩን እና የታሰሩትን የግፍ እስረኞች እንዲፈታ ጥሪ አድርገዋል።
Source: Link to the Post