“በድርጊቱ የሚጠበቀውን ያህል ካልተበሳጨን፣ ካላዘን፣ ካልተቆጣን፣ ለመፍትሔው በትጋት ካልተዘጋጀን ሕገ ወጥ ጵጵስናን እየተለማመድነው እንደሆነ ማሳያ ነው። አዎ ሕገ ወጥ ጵጵስናን እንደ ሰው…

“በድርጊቱ የሚጠበቀውን ያህል ካልተበሳጨን፣ ካላዘን፣ ካልተቆጣን፣ ለመፍትሔው በትጋት ካልተዘጋጀን ሕገ ወጥ ጵጵስናን እየተለማመድነው እንደሆነ ማሳያ ነው። አዎ ሕገ ወጥ ጵጵስናን እንደ ሰው ግድያና ቤት ፈረሳ አለማመዱን።” ሀብታሙ ይታየው_በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፊዚክስ እና የኦርቶዶክስ ቲዎሎጂ ተመራማሪ፣ አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ሀምሌ 18/2015 ዓ/ም_አዲስ አበባ ኢትዮጵያ ሕገ ወጥ ጵጵስናን እንደ ሰው ግድያና ቤት ፈረሳ አለማመዱን። ይህንም መሪዎቻችን ፖለቲከኛ ሆነው እያለ ለኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ሃይማኖት መስፋፋትና ለሕዝበ ክርስቲያኑ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ትምርተ ወንጌል መዳረስና መስፋፋት ያሰቡ መስለው አቀነቀኑት፤ ነገር ግን ድርጊታቸው ለፖለቲካቸው ማስፈጸሚያ፤ ኢትዮጵያን ፍርሰው ለራሳቸው የሚመቹ ሃይማኖት አልባ የሆኑ ትንንሽ አገራት ለመመሥረት ታቅዶ የተሰራ ነው። ለዚህም “ኢትዮጵያን ለማፍረስ ኢትዮጵያ የተመሰረተችበትን የኦርቶዶስ ቤተ ክርስቲያንን ማፍረስ ዋነኛና አይነተኛ መንገድ ነው።” ብለው ስላሰቡ ነው ይህን ጉዳይ ሳይታክቱ የሚደክሙበት። ኢትዮጵያ ውስጥ መጀመሪያ አንድ፣ ሁለት፣ ሦስት፣ ወዘተ ሰዎችን በማንነታቸው በአሰቃቂ ሁኔታ በመግደል አለማመዱን። ከዛም በጅምላ ሁለት መቶ፣ ሦስት መቶ፣ ወዘተ ሰዎች በማንነታቸው በጅምላ በአሰቃቂ ሁኔታ እየገደሉ በአንድ መቃብር በጅምላ በዶዘር እየቀበሩ እንድንለማመደው አደረጉን። ይህን ለሦስት ለአራት ዓመት ካለማመዱን በኋላ አሁን አንድ፣ ሁለት፣ ሦስት፣ ወዘተ ሰዎች ሲገደሉ ምንም የማይመስለን የማይደንቀን የማናዝን እንድንሆን ሆነን እንድንሰራ አደረጉን። በዚህም ያሰቡት ተሳካላቸው ያስብላል። ዛሬ ሰው ተገደለ ሲባል የሚደነቅ የሚገረም የለም። የሚያዝንም የለም። ለእልቅሶ የሚሔደው ሰው ቀንሷል። ስንት ሰው ተገደለ? ብለ ቁጥሩን የምንጠይቅ እንጂ ጉዳዩን የማናወግዝ፤ የማናዝን ሆን። ይህን ድርጊት መታገል ያለባቸው ፖለቲከኞች ናቸው ብለንም የተውነው ይመስላል። እኛን የማይመለከት ጉዳይ እስከሚመስለን ድረስ። ከዚህ በተጨማሪ በገጠር ያሉ ገበሬዎችን እየገደሉ፣ ከቀያቸው እያፈናቀሉ ሀብት ንብረታቸው ሲዘርፉ ሰማን። ለትንሽ ጊዜ ተገርመን አዘን። እየተደጋገመ ሲሔድ ግን ከሞት ጋር በማነጻጸር፤ ሰው እየተገደለ ባለባት አገር የንብረት መዘረፍ የማይጨንቀን ሆነ። ቤታቸው ሲቃጠል ከመጤፍ የማንቆጥረው ሆነ፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በተለይም አማራዎች ተሰደው ወደ አዲስ አበባና አማራ ክልል ሲገቡ ተለማምደነው የማያስጨንቀን ሆነ። የማንነት ግድያው፣ ከቤተ መፈናቀሉ፣ ሀብት ንብረት መዘረፉ ወደ አዲስ አበባ መጣ። እኛም እንደ መጀመሪያው ብዙ አልደነቀንም። ለምን? ተለማምደነዋል። በጥምቀት በዓል ከካህናት ከታቦታት ከምዕመናን ፊት ወጣቶች በደስታቸው ቀን በዓል ሲያከብሩ ተገደሉ። ቀድሰው ያቆረቡ ካህን ወደ ቤታቸው ሲሄዱ በጠራራ ፀሐይ በድንጋይ ተወግረው ተገደሉ። በጣም ከመለማመዳችን የተነሳ አሁንም ምንም አልመሰለንም። በአዲስ አበባ የቤቶች መፍረስ ከ120 ሺ በላይ ደረሰ። ከዚህ በላይ ይቀጥላል ተባልን አሁንም አይደንቀንም። ቤታቸው የፈረሰባቸው ሰዎች ወደ አማራና ወደ ደቡብ ክልል ተሰደዱ። እኛ በዚህ ሁሉ የማንነት መከራና ግፍ አንደነቅም፤ ለምን? አዲሳችን አይደለም፤ ተለማምደነዋል። ጉዳዩ በዚህ አላበቃም አዲስ አበባን የኦርምያ እንድትሆን ታገሉ፤ በትምህርት ቤቶች የኦሮሚያን ሰንደቅ ዓላማ በመስቀል የኦሮሚያን መዝሙር በተማሪዎች ዘንድ እንዲዘመር አደረጉ። የእኛ ሰዎች ትንሽ ታግለው የተሳካላቸው የሚመስለው ይህን ማስቆም መቻሉ ብቻ ነው። ዳሩ ቅሉ እነርሱ የአዲስ አበባን ግዛት ዙሪያውን በመቁረስ ሸገር ከተማ ብለው፤ ኦሮሞ ብቻ የሚኖርባት ከተማ ለመመስረት አቀዱ ይኸው እየተሳካላቸው ነው። ይህ ለምን አደረጉት። ቀስ በቀስ አዲስ አበባን የኦሮሚያ ለማድረግ መጀመሪያ በኦሮሚያ ሸገር ከተማ እንጠራት ብለው ተነሱ፤ በዚህ መልክ መፈጸም ጀመሩ። አሁን በሸገር ከተማ የሚኖሩ ኦሮሞ ያልሆኑ ሰዎች በተለይም አማራዎች ደቡቦች ነገ ምን ሊመጣባቸው እንደሚችል መገመት አይችሉም፤ እኛም አንችልም። አይበለው እንጂ አደጋ ቢመጣባቸው ማንም አያድናቸውም። ለመንግሥት አካላት ቢያመለክቱ፤ ለምን እዚህ ተቀመጣችሁ አትወጡም ነበር፤ ይህ እኮ የእናንተ ቦታ አይደለም? እንደሚባሉ ያውቁታል፤ በሁሉም ዘንድ ይታወቃል። የእኛ የሰው ግድያ እና የቤት ፈረሳ ልምምድ ቅጥ የለውም፤ እንኳን ታግለን ለማሸነፍ የሚያወራን ሰው ሥራ ፈት ይመስለናል። አንድ ሰው በዚህ ጉዳይ ካወራ፤ ለምን ወደ ፖለቲካ አስተሳሰብ ገባህ የሚለው ብዙ ነው። የእኛ ነገር የሚታገሉትን ከመርዳት ይልቅ ተስፋ ቆርጠው እኖዲተውት የምናደርግ ሰዎች እንበዛለን። ልክ እንዲሁ፡ ሕገ ወጥ የኤጲስ ቆጶሳትን ሢመት በዚህ ዓመት በጥር ፩፬ በኦሮሚያ፣ 3ቱ ጳጳሳት 26 የፖለቲካ ጳጳሳት በመሾማቸው፤ ደንግጠን እንድንጫጫ አደረጉን። በሲኖዶስ ተወገዙ፣ በጣም አዘን፣ ጥቁር ለብሰን ታላቅ ሱባኤ ገባን። የካቲት ፭ ሰልፍ ለማድረግ ተወሰነ። በጣም ደስ አለን። በአጻሩ በሻሸመኔ እና በሌሎች ከሕገ ወጥ ተሿሚ “ጳጳሳት” ጋር ግብግብ ተገጠመ፤ ከአርባ በላይ ወገኖቻችን ሰማዕትነትን ተቀበሉ። በመቀጠል ችግሩን ለመቅረፍ በሚመስል ከጠቅላዩ ጋር ግራ በገባውና የቤተ ክርስቲያንን ሕግ፣ ዶግማ፣ ቅኖና፣ ሥርዓትና ትውፊት ባልጠበቀ መልኩ እርቀ ሰላም አደረግን በማለት፤ ሿሚዎችም ተሿሚዎችም ይቅርታ ጠይቀው ይመጣሉ ተባለ። የይስሙላ ይቅርታ ጠይቀው አታለው መጡ፤ እኛም ምንም ማድረግ አልቻልንም፣ ትክክል አይደለም ብንልም የሚሰማን አልነበረም። ከሢመተ ኤጲስ ቆጶሳት በፊት፣ ሢመተ ኤጲስ ቆጶሳት ሒደትና አፈጻጸም መመሪያ በሊቃውንት (በኮሚቴ) ተዘጋጅቶ ለሲኖዶስ ቀረበ። ሲኖዶስም ይህን አልቀበልም ብሎ፤ እንደ በፊቱ በዘልማድ እፈጽማለሁ አለ። በዚህም የሊቃውንትንንና የሕዝበ ክርስቲያኑን አሳብ አልሰማም አለ። የሲኖዶስ አባላት አባቶቻችን ከእነዚህ አካላት በመንፈስ ተለየ። ይህን የሲኖዶስ ድርጊት ትክክል አይደለም ብለው ሕዝቡን ያስተማሩ መምህራን ብዙዎቹ ታሰሩ፤ የማኅበሩ ቴሌቪዥን ይህን ጉዳይ (የኮሚቴውን አሳብ) አስተላልፈሃል ተብሎ ለቀናት ተዘጋ። ሲኖዶስ በራሱ አሳብ ብቻ (የሊቃውንትን፣ የመምህራን፣ የካህናትንና የምዕመናንን አሳብ ሳይጨምር)፣ የእነ አቢይ አህመድንና የሽመልስ አብዲሳን አሳብ ብቻ ለማስተናገድ ተዘጋጀ፤ በጉባኤው ሰባት ለኦሮምያ፣ ሁለት ለደቡ፣ አጠቃላይ ዘጠኝ ብቻ እንሾማለን ተብሎ ተወሰነ። ሐምሌ ፱፡ ፪ሺ ፩፭ ዓ.ም የቤተ ክርስቲያን ሕግ፣ ዶግማ፣ ቅኖና፣ ሥርዓትና ትውፊት ተሽሮ የኤጲስ ቆጶሳት ሢመት ተፈጸመ። ይህም በሲኖዶስ ታሪክ ተደርጎ የማያውቅና የፖለቲካ ጳጳሳት ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ያልሆነ ለፖለቲካ አገልግሎት የተፈጸመ ነው ተብሎ በታሪክ እንደሚመዘገብ ይገመታል። ለእኛም ድርጊቱ አዲስ ነገር ስለሆነ በጣም አዘን። ለነገሩ የኦሮሚያ ቤተ ክህነት እያሉ ከሁለት ዓመት በፊት ሲበጠብጡን ትንሽ ታግለን የተውት መስሎን ተመልሰን ወደ ቤታችን ገብተን ተኛን። እነርሱ ግን የዛሬው “የኦሮሚያ የብሔር ብሔረሰቦች ቤተ ክህነትና መንበር” ምሥረታ ላይ ደረሱ። ይኸው ሕገ ወጥ ናችሁ ተብለው ቢወገዙ ዛሬም “ጳጳስ” ነን ብለው በማን አለብኝነት እየወጡ ሕጋዊ ነን እያሉ መግለጫ እየሰጡ ይገኛሉ። ለምሳሌ “ብጹዕ አባ ገብርኤል” ነኝ ባዩ ሕገወጥ። ምክንያታቸው ጥር ፩፬ የተሾምነ ሁላችንም በሲኖዶስ ጸድቆልን ለመቀጠል ነው የተስማማነው እኝጂ ከኛ ውስጥ ሦስት ብቻ ልትሾሙ (ልትቀበሉ) አይገባም የሚል ነው። እንዲሁም ጵጵስና ሁለት ጊዜ ሊፈጸም አይገባም ብለውም የእነሱ ሕገ ወጡ ሢመት ትክክል ነው መደገም የለበትም ብለው ያምናሉ። ይህን ውዝግብ ጠቅላይ ቤተ ክህነትም መንግሥትም እንዳላዩ ሲያልፉት እየታየ ነው። ይህ ጉዳይ ነገ ምን ሊሆን ይችላል? የሚለውን ማንም መገመት አይችልም። በዚህ ሀዘናችን ሳንጽናና ሌላ የትግራይ ቤተ ክህነት “መንበረ ሰላማ” የሚል ነገር መስማት ጀመርን። በፖለቲካ የሚዘወር እንደሆነ ሁሉም ገብቶታል። ተለማመድነው መሰለኝ እንደ ጥር ፩፬ የኦሮሚያው ብዙም አልደነገጥንም። የሚገርመው እነዚህ በድብቅ ከተከናወነው ከኦሮሚያው በተለየ መልኩ ቀድመው በመግለጫ በትግራይ ቤተ ክህነት “መንበረ ሰላማ” እንደሚመሰርቱ እና በእቅዳቸው መሠረት በቅደም ተከተል እየነገሩን የመጡ ሲሆን በሙሉ ድፍረ መስራታቸውን ስናይ በግልጽ የመንግሥት እጅ እንዳለበት ማንኛውም ሰው በቀላሉ እንደተረዳው እገምታለሁ። ከሳምንት በፊት በእቅዳቸው መሠረት አሥር ( አምስቱ ለትግራይ አምስቱ ለባህር ማዶ አገራት) ሕገ ወጥ ኤጲስ ቆጶሳት እንደሚሾሙ መርጠው ስማቸውን ነገሩን። ትናንት ቅዳሜና እሁድ ሐምሌ ፩፮ የስድስቱን “ሢመተ ጵጵስና” ፈጸሙ። የአራቱ በባህር ማዶ አገራት በቅርብ ይፈጸማል ተብሎ ይጠበቃል። ከኦሮምያው ይልቅ የትግራዩ ብዙ ድብልቅልቅ ነገር ታይቶበታል። ቅዱስነታቸው የእርቀ ሰላሙ ልዑክ መሪ ሆነው ወደ ትግራይ በሔዱ ጊዜ የእግዚአብሔርን ቤት፣ በበላይነት እርሳቸው የሚመሯትን የቤተ ክርስቲያን በር በእነዚህ ጳጳሳት ተዘግቶባቸው ገብተው ጸሎት እንዳያደርጉ ተከልክለው ተመልሰዋል። ለእርቀ ሰላምም አንቀመጥም ብለው በከንቱ ተመልሰዋል። ሕገ ወጡ ሢመተ ጵጵስና በሐምሌ ፱ በሲኖዶስ የተፈጸመውን በሚመስል በተግባርና በቅደም ተከተል ፈጽመውታል። ትግራይ የኦርቶዶክስ መሠረት ስለሆነች እንዲህ ይደረጋል ብለው ያላሰቡ ሰዎች ይህ ሲፈጸም በጣም ደንግጠዋል። በአንጻሩ ደግሞ በፖለቲከኞች የተጸነሰሰ ስለሆነ ያሰቡትን እንደሚፈጽሙ ቀድመው ያወቁ ሰዎች ብዙም አልገረማቸውም፤ አልደነቃቸውም። አንዱ ድብልቅልቅ ስሜት ይህ ነው። ነገር ግን ከኦሮሚያው ድርጊት ጋር ሲነጻጸር የሕዝበ ክርስቲያኑ ቁጣ በትግራዩ የቀነሰ ነበር ማለት ይቻላል። በድርጊቱ የሚጠበቀውን ያህል ካልተበሳጨን፣ ካላዘን፣ ካልተቆጣን፣ ለመፍትሔው በትጋት ካልተዘጋጀን ሕገ ወጥ ጵጵስናን እየተለማመድነው እንደሆነ ማሳያ ነው። አዎ፡ ሕገ ወጥ ጵጵስናን እንደ ሰው ግድያና ቤት ፈረሳ አለማመዱን። አንድ ሰው፡ “ማንው ባለ ሳምንት ሕገ ወጥ ጵጵስና የሚደረግበት ክልል?” ብሎ ቢጠይቅ እንደ ጥፋተኛ ይቆጠር ይሆን። እኔ በበኩሌ እንደ ጥፋተኛ አልቆጥረውም። ይህ ሰው በኢትዮጵያ ምድር ይሆናል ተብሎ የማይገመተው ሕገ ወጥ ጵጵስና በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ላይ በትቂት ወራት ልዩነት ሁለት ጊዜ ሲደረግ አይቷልና ይህን መጠየቁ ጥፋተኛ አያስብለውም። በተጨማሪ የሕዝበ ክርስቲያኑ ቁጣ ከመጀመሪያው ይልቅ በሁለተኛው በጣም ቀንሶ አይቶታልና። አንድ አካል ይህን በሌሎች ክልሎች ለመፈጸም ቢነሳ ትክክል አይደለም ብሎ የሚቃወመው ሕዝብ ትንሽ ስለሚሆን (ከሁለተኛው በጣም ስለሚቀንስ)፤ ጉዳዩን እጅግ በጣም ስለተለማመድነው የሕዝቡ ቁጣ በጣም እንደሚበርድ ስለሚገመት ይህ እንዲሆን የሚያስቡ አካላት ቢነሱ በቀላሉ መፈጸም ይቻላሉ ማለቱ ስለሆነ በእኔ እይታ ትክክል ነው። ስለሆነም የዚህ ሰው ማን ነው ባለሳምንት ጥያቄ መክኖ እንዲቀር (ሀ) ቅዱስ ሲኖዶስ፣ (ለ) የሊቃውንት ጉባኤ፣ (ሐ) የሊቃውንት፣ የመምህራን፣ የካህናትና የምዕመናን ኅብረት ተናበው በአንድነት ጠንክረው ለመሥራትና የመጣውን የቤተ ክርስቲያን የኅልውና አደጋ ለመመከት መዘጋጀት አለባቸው። በተለይም አሁን ሕገ ወጥ ጵጵስናን እንደ ሰው ግድያና ቤት ፈረሳ እያለማመዱን ባለበት ሰዓት በ(ሐ) የተጠቀሱት አካላት በተጠንቀቅ ቁመው የቤተ ክርስቲያንን ኅልውና ከኛ ውጭ የሚታደግ የለም ብለው እስከ መስዋእትነት በመዘጋጀት መታገል ይኖርባቸዋል። ምክንያቱም (ሀ)ና (ለ) በውጭዊ አካል ተደነቃቅፈው የሚጠበቅባቸውን ማድረግ እንደማይችሁ ታይተዋልና። ሕገ ወጥ ጵጵስናን እንደ ሰው ግድያና ቤት ፈረሳ አለማመዱን።

Source: Link to the Post

Leave a Reply