በጉራጌ ዞን ለ3ተኛ ጊዜ የሥራ ማቆም አድማ መደረጉ ተሰማ

አርብ ኀዳር 9 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የጉራጌ ዞን ነዋሪዎች የምክር ቤት የስብሰባ ጥሪ እንደሚደረግ ደብዳቤ መላኩን ተከትሎ የሥራ ማቆም አድማውን ለሦስተኛ ጊዜ ማድረጋቸው በደቡብ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ክልል የ 2013/14 ተመራጭ የምክር ቤት አባል እና የጉራጌ ክልል ተወካይ ታረቀኝ ደግፌ ተናግረዋል።

የዛሬው የሦስተኛ ዙር አድማው ለአንድ ቀን የሚቆይ ሲሆን፤ ንግድ ቤቶች፣ መንገዶች ሲዘጉ የባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎች እንዲሁም ሌሎች የትራንስፖርት አገልግሎቶች ተቋዋርጠዋል። የመስረታዊ አገልግሎቶች የአምፑላንስ፣ የጤናና ሌሎች ለማህበረሰቡ አስፈላጊ ናቸው የሚባሉ አገልግሎቶች ክፍት እንዲሆኑ መደረጉን ተናግረዋል።

የአድማው አላማ የሆነውም የጉራጌ ዞን ህዝቦች ህዳር 17 ቀን 2011 በዞኑ ምክር ቤት በሙሉ ድምጽ የአደረጃጀት ጥያቄ እንፈልጋለን የሚለውን ጥያቄ ምላሽ በተመለከተ በክላስተር ተደራጁ በሚል ሃሳብ በመቀረቡ ሲሆን፤ ይህም የክላስተር አደረጃጀት ሃሳብ 52 ድምጽ ተቃውሞ ውድቅ ቢሆንም እስካሁን ተግባራዊ አለመደረጉ ቅሬታ በመፍጠሩ ነው ተብሏል።

ይህ መሆኑን ተከትሎ ሃሳቡን ተቃውመዋል የተባሉ አመራሮች እንዲሁም ወጣቶች የመታሰር እጣ እንደደረሰባቸውም አንስተዋል። አሁን ላይ የክላስተር አደረጃጀት ሃሳቡን በድጋሚ ምክር ቤት አምጥቶ ለማጸደቅ እንቅስቃሴ መጀመሩን ተከትሎ የቤት መቀመጥ አድማው ተግባራዊ መደረጉን ታረቀኝ ጨምረው ተናግረዋል ሲል ብስራት ሬዲዮ ዘግቧል።

በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች ህዝቦች ክልል በ2008 በተሻሻለው የምክርቤት አዋጅ አንድ ጉዳይ በአንድ አመት ውስጥ ውድቅ ከሆነ በበጀት ዓመቱ ዳግም አይታይም።

በተጨማሪም የሥራ ማቆም አድማ መደረጉ አስመልክቶ፤ በወልቂጤና አካባቢዋ ትናንት ሐሙስ ኀዳር 8 ቀን 2015 የሥራ ማቆም አድማ ጥሪ ወረቀቶች መበተናቸው የተሰማ ሲሆን፤ ይህንን ተከትሎ በዛሬው ዕለት በከተማዋ ቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ መደረጉን የሚያሳዩ ምስሎች በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ሲዘዋወሩ ተስተውሏል።

The post በጉራጌ ዞን ለ3ተኛ ጊዜ የሥራ ማቆም አድማ መደረጉ ተሰማ first appeared on Addis Maleda.

Source: Link to the Post

Leave a Reply