በጉራጌ ዞን በታጠቁ ኃይሎች አምስት ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ በአካባቢው ውጥረት ነግሷል

ማክሰኞ ሰኔ 27 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በደቡብ ክልል በጉራጌ ዞን በምስራቅ መስቃን ወረዳ እሁድ ሰኔ 25/2015 ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች በተሰነዘረ ጥቃት ሦስት ተማሪዎች እንዲሁም እናትና ልጅ መገደላቸውን ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በዕለቱ ተማሪዎቹ የተገደሉት ምሽት ሦስት ሰዓት ገደማ የስምንተኛ ክፍል ሚኒስትሪ ፈተና ለመፈተን እያነበቡ በነበረበት በመኖሪያ ቤታቸው ነው ተብሏል፡፡

ታጣቂዎቹ ሦስቱን ተማሪዎች ከገደሉ በኋላ፤ የአካባቢው ማህበረሰብ በጩኸት ሲከተላቸው በቼ ቀበሌ ውስጥ የምትኖር አንዲት እናትን ከእነልጇ ገድለው ከአካባቢው መሰወራቸውን ነው ነዋሪዎች የገለጹት።

በዚህም በዞኑ የሚገኙት መስቃንና ማርቆ ብሄረሰቦች መካከል የቆየ አለመግባባት ከመኖሩ ጋር ተያይዞ “ተማሪዎቹ በማርቆ ብሄረሰብ ተወላጆች የተገደሉ ናቸው” በሚል በኹለቱ ብሄረሰቦች መካከል ውጥረት መንገሱ ተነግሯል።

በአሁኑ ወቅት በምስራቅ መስቃን ወረዳ ሥር የሚገኙ ዘጠኝ ቀበሌዎች፤ በመስቃንና በማረቆ ብሄረሰቦች መካከል በይገባኛል ጥያቄ ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ ተመላክቷል።

ይህን ተከትሎም እሁድ ሰኔ 25/2015 ምሽት በተገደሉት ሦስት ተማሪዎች ምክንያት፤ በኹለቱ ብሔረሰቦች መካከል ውጥረት ነግሷል ነው የተባለው።

ተማሪዎቹ ከተገደሉበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ትናንት ሰኔ 26/2015 ከቀኑ አምስት ሰዓት ድረስም በአካባቢው ከፍተኛ የተኩስ ድምጽ እንደሚሰማም ነው የተጠቀሰው።

የተፈጠረውን ችግር ለማረጋጋት ወደ ቦታው ከፍተኛ የመንግሥት የጸጥታ አካላት እየገቡ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ ይሄ ዘገባ እስከትጠናቀረበት ሰዓት ድርስ በአካባቢው ያለው ውጥረ እንደቀጠለ መሆኑ ተመላክቷል።

የጉራጌ ዞን ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ጠጄ መሀመድ “እኛም ጉዳዩን ሰምተን ለማረጋጋት ወደ አካባቢው እየሄድን ነው፡፡” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸው፤ ተጨማሪ ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply