
በጋምቤላ ክልል በታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት አራት ሰዎች መገደላቸው እና ከአራት ሰዎች በላይ መቁሰላቸው ተገለጸ በጋምቤላ ክልል ማጃንግ ዞን ጎደሬ ወረዳ፣ ጉሽሜ ተብሎ በሚጠራ ቦታ ባለፈው እሁድ ነሐሴ 29/2015 ምሽት ሦስት ሰዓት ገደማ በአንድ ቤት የነበሩ አራት ሰዎች ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች በተፈጸመ ጥቃት መገደላቸውንና ከአራት በላይ ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን የማጃንግ ብሔረሰብ ዞን አስተዳደር ለአዲስ ማለዳ ገልጿል፡፡ የማጃንግ ብሔረሰብ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኤሊያስ ገዳሙ፤ “በጎደሬ ወረዳ ውስጥ ጉሽሜ እና አካቺኒ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በአንዲት የሳር ቤት የነበሩ አራት ሰዎች ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች በመገደላቸው በአካባቢው ብሔር ተኮር ውጥረት ነግሷል።” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡ ማንነታቸው ያልታወቁት አካላት ጥቃቱን የፈጸሙት ጨለማን ተገን አድረገው በመሆኑ እስካሁን በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ማዋል እንዳልተቻለ የገለጹት አስተዳዳሪው፤ ጥቃቱን በፈጸሙበት ቅጽበት በአካባቢው የጸጥታ አካላት ባለመኖራቸው ጥቃቱን መቆጣጠር ሳይቻል መቅረቱን ተናግረዋል፡፡ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አክለውም፤ የተገደሉትን ሰዎች አስከሬን ማክሰኞ ነሐሴ 30/2015 በአካባቢው የቀብር ሥነ ስርዓታቸው ከተፈጸመ በኋላ፤ የአካባቢው ነዋሪዎች “መንግሥት ይወቅልን” በማለት የተቀበሩትን ሰዎች አስከሬን አውጥተው ወደ መጃንግ ዞን እና ጎደሬ ወረዳ መውሰዳቸውን ገልጸዋል። በዚህም “ነዋሪዎቹ ገጀራ እና የጦር መሳሪያ ይዘው ስለነበር ሌላ ተጨማሪ ችግር ፈጥረዋል።” ያሉት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ፤ “የአካባቢውን ነዋሪዎች የአገር ሽማግሌዎችና የፖሊስ አባላት ለማረጋጋት ቢሞክሩም ከአቅም በላይ በመሆኑ የፌደራል ፖሊስና የመከላከያ ሠራዊት አባላት ገብተው እንዲያረጋጉ አድርገናል።” ብለዋል፡፡ “ቢሆንም ግን ገጀራ እና የጦር መሳሪያ ይዘው የወጡት ሰዎች በአካባቢው የሚኖሩ ሌሎች ነዋሪዎችን ሲያገኙ በገጀራ ለመምታት እና ችግሩ ብሔር ተኮር እንዲሆን ሙከራ አድረገዋል።” ካሉም በኋላ፤ በዚህም ማክሰኞ ዕለት ኹለት ሰዎች በገጀራ በተፈጸመባቸው ጥቃት መቁሰላቸውን ገልጸዋል፡፡ በጎደሬ ወረዳ የተፈጠረውን ችግር የብሔር ተኮር ለማድረግ ሙከራ የሚያደርጉ አካላት መኖራቸውን ተከትሎም፤ ከባለፈው እሁድ ነሐሴ 29 እስከ ትናንት ጳጉሜ 01/2015 ድረስ በጎደሬ ወረዳ ዋና ከተማ ሜጢ ውስጥ ውጥረት መንገሱን ጠቁመዋል፡፡ ዋና አስተዳዳሪው አክለውም፤ “ችግሩ ወደ ብሔር ግጭት እንዳያመራ እና ተጨማሪ የሰው ሕይወት እንዳይጠፋ እንዲሁም ጥቃት የፈጸሙ አካላትን ማንነት ለማወቅና ወደ ሕግ ለማቅረብ ከፌደራል ፖሊስ እና ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በጋራ እየሰራን ነው።” ሲሉ ተደምጠዋል። በክልሉ ዋና ከተማ ጋምቤላ ከወር በፊት በተፈጠረ ግጭት የብዙ ሰዎች ሕይወት ማለፉ የሚታወስ ነው። #አዲስ ማለዳ አዳዲስ መረጃዎች አሻራ ሚዲያ የአይበገሬዎቹ ልሳን:- //Youtube:- Ashara Tv – https://www.youtube.com/channel/UC2LZu_N0iOJipVUw3RyR4Ng //https://www.facebook.com/asharamedia24 //ቴሌግራም:- https://t.me/asharamedi
Source: Link to the Post