በጋምቤላ ክልል አኝዋክ ብሔረሰብ ዞን ዲማ ወረዳ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት በተያዘው ሐምሌ ወር ብቻ 15 ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ለአዲሰ ማለዳ ገልጸዋል።
ጥቃቱን የፈጸሙት ከደቡብ ሱዳን ተነስተው ወደ ዲማ ወረዳ የገቡ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች መሆናቸውን የጠቆሙት ነዋሪዎቹ፤ ሐምሌ ወር ከገባ ጀምሮ እያደረሱት ያለው ጥቃት ተባብሶ መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡
ከደቡብ ሱዳን ተነስተው ወደ ክልሉ የሚገቡ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች የአካባቢውን ነዋሪዎች ከመግደል ባለፈ፤ መኖሪያ ቤቶችን እንደሚያቃጥሉና የቁም እንስሳቶችን እንደሚዘርፉም ተጠቅሷል።
ታጣቂዎቹ ከአኝዋክ ብሔረሰብ ዞን በተጨማሪ በኑዌር ዞን በሚገኙ ወረዳዎች ጥቃት እያደረሱ ነው የተባለ ሲሆን፤ በኢታንግ ወረዳ ባለፈው ግንቦት ወር ኹለት ሰዎች መገደላቸው ተመላክቷል።
እንዲሁም ባለፈው ሀሙስ ሐምሌ 06/2015 ከኢታንግ ወረዳ ወደ ጋምቤላ ከተማ ሲጓዝ በነበረ የሕዝብ ማመላሻ አውቶቡስ ላይ ታጣቂዎች በከፈቱት ጥቃት ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ንጹሃን መገደላቸውንም የዓይን እማኞች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
በተለይ ዲማ ወረዳ ከደቡብ ሱዳን እና ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ከጉራ ፈረዳና ሱርማ ወረዳ ጋር የሚዋሰን በመሆኑ፤ በወረዳው በልዩ ልዩ ሥም የሚንቀሳቀሱ ሽፍቶች መኖራቸውን ተከትሎ በየዕለቱ ጥቃት እንደሚፈጸም ነው ነዋሪዎች የተናገሩት።
ባለፈው ግንቦት 17/2015 ሦስት የአኝዋክ ብሔረሰብ ዞን ነዋሪዎች በታጣቂዎች በመገደላቸውም “ግድያውን የፈጸሙት የኑዌር ብሔረሰብ ተወላጆች ናቸው” በሚል በኑዌር እና በአኝዋክ ብሔረሰቦች መካከል ውጥረት እንደነበርም ተጠቁሟል።
በዚህም በኹለቱ ብሔረሰቦች መካከል ግጭት መቀስቀሱን ተከትሎ፤ የአካባቢው ነዋሪዎች ተፈናቅለው ወደ ክልሉ ዋና ከተማ ጋምቤላ እየገቡ መሆኑን መረዳት ተችሏል።
ከደቡብ ሱዳን ከሚመጡ የሙርሌ ጎሳዎች በተጨማሪ በኑዌር እና በአኝዋክ ብሔረሰብ ዞን የሚንቀሳቀሱ ሌሎች ታጣቂዎች እንዳሉ የጠቆሙት ነዋሪዎቹ፤ ንጹሃንን ከመግደል በተጨማሪ ንብረት ማቃጠልና መዝረፉም እንደቀጠለ ነው ብለዋል።
አዲስ ማለዳ ከጋምቤላ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ በጉዳዩ ዙሪያ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በተደጋጋሚ ብትደውልም ስልክ ባለመነሳቱ ምክንያት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
Source: Link to the Post