በጋምቤላ ክልል ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተከሰቱ ግጭቶች፤ ቢያንስ 138 ሰዎች መገደላቸውን ኢሰመኮ አስታወቀ 

በተስፋለም ወልደየስ

በጋምቤላ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ በተካሄዱ ግጭቶች፤ ቢያንስ 138 ሰዎች መገደላቸውን እና በ113 ሰዎች ላይ ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ። በግጭቶቹ የተነሳ በርካታ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን፣ መኖሪያ ቤቶች እና ንብረቶች መቃጠላቸውን እንዲሁም ዘረፋ መፈጸሙን ኮሚሽኑ ገልጿል።

ብሔራዊው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ይህን የገለጸው፤ ካለፈው ዓመት ግንቦት ወር ጀምሮ እስከ ጥር 2016 ዓ.ም በጋምቤላ ክልል የተከሰቱ ግጭቶችን ከመረመረ በኋላ ባወጣው ሪፖርት ነው። ዛሬ ረቡዕ የካቲት 20፤ 2016 ይፋ የተደረገው ይህ የምርመራ ሪፖርት፤ ተደጋጋሚ ግጭቶች ያስተናገደው የኢታንግ ልዩ ወረዳን ጨምሮ በጋምቤላ ወረዳ፣ በጎግ ወረዳ እና በጋምቤላ ከተማ የተከሰቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የዳሰሰ ነው። 

ኢሰመኮ ሪፖርቱን ለማዘጋጀት፤ ግጭት ወደተከተሰባቸው ቦታዎች በአካል በመሄድ ከተጎጂዎች፣ ከተጎጂ ቤተሰቦች፣ ከአይን ምስክሮች ከሀገር ሽማግሌዎች እና ከሃይማኖት መሪዎች ጋር ቃለ መጠይቆች እና የቡድን ውይይቶች ማድረጉን ገልጿል። በመንግስት የተወሰዱ እርምጃዎችን በተመለከተ፤ በየደረጃው የሚገኙ የጋምቤላ ክልል መንግስት የጸጥታና አስተዳደር አካላትን እንዲሁም የፌዴራል ተቋማትን በማነጋገር መረጃዎችን እና ማስረጃዎችን ማሰባሰቡንም በሪፖርቱ አመልክቷል።   

ከእነዚህ የመስክ ምልከታዎች በኋላ ተጨማሪ ክትትሎች በማድረግ በኮሚሽኑ የተዘጋጀው ባለ 15 ገጽ ሪፖርት፤ የግጭቱን መነሻ እና ከዚያ በኋላ በነበሩት ጊዜያት በተለያዩ አካባቢዎች የደረሱ ጥቃቶች፣ ግጭቶች እና ጉዳቶችን በዝርዝር የያዘ ነው። በጋምቤላ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በየጊዜው ለሚያገረሽው ግጭት በመነሻነት የተጠቀሰው በግንቦት 2015 ዓ.ም. በኢታንግ ልዩ ወረዳ የተፈጠረ ክስተት ነው።  (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ ይታከልበታል]

Source: Link to the Post

Leave a Reply