በጋምቤላ ክልል ከ33 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነቡ ሶስት የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተመርቀው ለአገልግሎት በቁ

በጋምቤላ ክልል ከ33 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነቡ ሶስት የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተመርቀው ለአገልግሎት በቁ

አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2013 (ኤፍቢሲ) በጋምቤላ ክልል በመንገሺና በዲማ ወረዳዎች ከ33 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነቡ ሶስት የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት በቅተዋል፡፡

የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ላክዴር ላክባክ የውሃ ፕሮጀክቶቹን በመረቁበት ወቅት ቀደም ሲል ተጀምረው በተለያዩ ምክንያቶች ያልተጠናቀቁ የልማት ፕሮጀክቶች ለህብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

ክልሉ እጅግ ከፍተኛ የሆነ የገፀ-ምድርና የከርሰ-ምድር የተፈጥሮ ውሃ ባለቤት ቢሆንም የክልሉ ህዝብ ተጠቃሚ ያለመሆኑን ጠቅሰው የተመረቁትን የውሃ ፕሮጀክቶች ጨምሮ በጅምር ላይ ያሉት ሲጠናቀቁ የህብረተሰቡን ችግር ከመቅረፍ አንፃር ፋይዳቸው የጎላ እንደሚሆን አመልክተዋል፡፡

በፕሮጀክቶች ዙሪያ የሚስተዋሉ የአፈፃፀም ክፍተቶችን ለመቅረፍ የግል ባለሀብቶች፣ የመላው ህብረተሰብና የአጋር አካላት ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚኖርበት አስታውቀዋል፡፡

የክልሉ ውሃና መስኖ ልማት ምክትል ኃላፊ አቶ አቡላ ኞች በበኩላቸው በጎደሬ ሚሽን፣ በኮይ እና በዲማ ከተማ የተመረቁት የውሃ ፕሮጀክቶች በአንድ ቋት የንፁህ መጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮግራም ከ88 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ እየተገነቡ ከሚገኙት 71 የውሃ ፕሮጀክቶች መካከል እንደሆኑ ጠቅሰዋል፡፡

ግንባታቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት የበቁት የጎደሬ ሚሽን የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት 8 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር፣ የዲማ ከተማ መጠጥ ውሃ ማስፋፊያ 17 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር እንዲሁም የኮይ ቀበሌ አዲስ ግንባት 7 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር እንደፈጀ ገልፀዋል፡፡

በመንግስትና በባለድርሻ አካላት ከፍተኛ መዋዕለ-ንዋይ የፈሰሰባቸው የውሃ ፕሮጀክቶች ቀጣይነት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡ የአካባቢው ህብረተሰብ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ግዴታቸውን መወጣት እንደሚኖርባቸው አብራርተዋል፡፡

አንዳንድ የጎደሬ ሚሽን፣ የኮይና የዲማ ከተማ ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት የተመረቀው የውሃ ፕሮጀክት ቀደም ሲል የነበረውን ከፍተኛ የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር እንደሚያቃልልላቸው ገልፀዋል፡፡

የውሃ ፕሮጀክቶቹ ረጅም ጊዜ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን የጠቀሱት ነዋሪዎቹ ፕሮጀክቶቹ በስኬት እንዲጠናቀቁ አስተዋጽዖ ላበረከቱ አካላት ምስጋናቸውን ማቅረባቸውን ከጋምቤላ ክልል ፕሬስ ሴክሬተርያት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

 

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

The post በጋምቤላ ክልል ከ33 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነቡ ሶስት የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተመርቀው ለአገልግሎት በቁ appeared first on Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C.

Source: Link to the Post

Leave a Reply