ምክር ቤቱ ይህ መርህ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥም ቢሆን እንዲከበር ጠይቋል፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት በሥነ ምግባር የታነጸ በሃላፊነት ስሜት ህዝብን የሚያገለግል ሚዲያ በሀገራችን እንዲጎለብት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጾ፣ በሕግ ተመዝግበው ፈቃድ የወሰዱ የህዝብ ፤የንግድ፤ የማህበረሰብ መገናኛ ብዙሃንን፤የበይነ መረብ ሚዲያንና የጋዜጠኞች ሙያ ማህበራትን በአባልነት በማቀፍ የእርስ በእርስ የቁጥጥር ስርዓትን ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝ ተናግሯል፡፡
ምክር ቤቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትና ጋዜጠኞች ላይ ከህግ አግባብ ውጪ አስሮ የማቆየትና ለስርጭት የተዘጋጀ የህትመት ውጤትን የማገድ ድርጊቶች እንደተፈፀመባቸውና በዚህም ሳቢያ ተቋማቱ የእለት ተዕለት ስራዎቻቸውን ለመስራት መቸገራቸውን ከደረሱት ሪፖርቶች መገንዘቡንም አስታውቋል፡፡
ከሕገ መንግስቱ ጀምሮ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን ጥበቃ ለማድረግ የወጡ የሕግ ድንጋጌዎች ቢኖሩም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በሀገሪቱ ህግ መሠረት ተመዝግበውና ፍቃድ አውጥተው የሚሰሩ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ጋዜጠኞችና የህትመት ውጤት በፀጥታ ሃይሎች ከህገ አግባብ ውጪ መታገታቸው አሳስቦኛል ነው ያለው፡፡
እንደ አብነትም በኢትዮ ሃበሻ አሳታሚ ድርጅት በየሳምንቱ እየታተመ የሚሰራጨው ጊዮን መፅሄትና ዋና አዘጋጁ ነሃሴ 19 ቀን 2015 በፖሊስ በቁጥጥር ስር ውለው ከአንድ ሳምንት በሃላ ዋና አዘጋጁ ያለ ክስ ሲለቀቅ መፅሄቱ ከአንድ ወር ከ 15 ቀን በላይ አልተለቀቀም፤
የትርታ ኤፍ ኤም 97.6 የፕሮግራም ዳይሬክተር ጳጉሜ 5 ቀን 2015 ከመኖሪያ ቤቱ በጥፀታ ሃይሎች ከተወሰደ በሃላ ከአንድ ወር ከ20 ቀናት በላይ ክስም አልተመሰረተበትም፤ፍርድ ቤትም ሊቀርብ አልቻለም፤
በመናኛ ብዙሃን አዋጅ ቁጥር 1238 አንቀጽ 85 /7 ላይ በግልጽ እንደተደነገገው በየጊዜው የሚወጣ ህትመት ከመሰራጨቱ በፊት በጽጥታ አካላት የሚሰጥ የእገድ ትዕዛዝ የትዕዛዙ መነሻ የሆነውን አንቀጽ ወይም አንቀጾች፣ የህትመቱን ቅፅ፣ ጽሁፉ የወጣበትን እትም መገለጽ አለበት፡፡ እገዳውም ለሥርጭት በተዘጋጁ ህትመቶች ላይ ብቻ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡> ሲል ይደነግጋል፡፡
ሆኖም ጊዮን መጽሄት በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋለበት ጊዜ አንስቶ በአዋጁ መሰረት ተመርምሮ የጋረጠው አደጋ ስለመኖሩ ያልተረጋገጠ ሲሆን ለፍርድ ቤትም በ48 ሰአት ውስጥ የቀረበ ክስ የለም፡፡
በሌላ በኩል በመገናኛ ብዙሃን አማካይነት የወንጀል ድርጊት በመፈፀም የተጠረጠረ ማንኛውም ሰው ወይም አካል በወንጀል ሥነ-ሥርዓት የሕግ ድንጋጌዎች መሠረት ለተጨማሪ ምርመራ በእስር እንዲቆይ ሳይደረግ ክሱ በቀጥታ በዓቃቤ ሕግ አማካኝነት ለፍርድ ቤት መቅረብ እንዳለበት በመገናኛ ብዙኃን አዋጁ 1238/13 አንቀፅ 86 ንዑስ አንቀፅ 1 ላይ በግልፅ ቢደነገግም የትርታ ኤፍ ኤም ጋዜጠኛ ግን ከአዋጁ ተቃራኒ በሆነ መልኩ ለሳምንታት ያለ ክስ በእስር ላይ ይገኛል ብሏል።
በአስቸካይ ጊዜ አዋጅ ውስጥም ቢሆን በጋዜጠኞችና በመገናኛ ብዙሃን ተቀማት ላይ የሚኖር ተጠያቂነት በህጉ አግባብ ብቻ መከናወን ይኖርበታል ብለን እናምናለን ያለው ምክር ቤቱ፤ ይህ እለመሆኑ ግን ሀገሪቱ በአለም አቀፍ ደረጃ ያላት ገፀታ ላይ ጥላ የሚያጠላ ይሆናል ብሏል፡፡
ላለፉት አምስት ዓመታት የፍትህ አካሉ የተለያዩ ማሻሻያዎች እየተደረጉበት ያለ ቢሆንም ጋዜጠኞችንና ተቋማቱን በተመለከተ በሕጉ አግባብ ተደጋጋሚ የመብት ጥሰቶችን ለማስቀረት ያለመቻሉ በእጅጉ እንደሚያሳስበው ምክር ቤቱ አስታውቋል፡፡
በመሆኑም መንግስት የወንጀል ተግባሮችን የመከላከል፣ የመመርመር እና ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ የፍትሕ ሥርዓቱ በአስቸካይ ጊዜ አዋጅ ድንጋጌ ውስጥም ቢሆን በጋዜጠኞችና በመገናኛ ብዙሃን ተቋማቱ ላይ የሚፈፀሙ የመብት ጥስቶችን በህጉ አግባብ ብቻ እንዲመራ በማድረግ ህገ ወጥ የወንጀል ድርጊቶችን በተቻለ ፍጥነት በማረም ሕገመንግስታዊ ግዴታውን እንዲወጣ ምክር ቤቱ ጠይቋል፡፡
ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ጥቅምት 12 ቀን 2016 ዓ.ም
Source: Link to the Post