በጎንደር በሚተኮስ ተባራሪ ጥይት ሰዎች እየተገደሉና እየቆሰሉ ነው ተባለ

አርብ ግንቦት 4 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በአማራ ክልል በጎንደር ከተማ አስተዳደርና አካባቢዋ በየወቅቱ የሚያጋጥመው የጥይቅ ተኩስ የንፁሃንን ሕይወት እየቀጠፈ ነው ሲሉ ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።

የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ እንደገለጸት፤ የጥይት ተኩስ በከተማዋ እየተበራከተ በመምጣቱ ከሚያዚያ ወር ጀምሮ እስከ ረቡዕ ግንቦት 2/2015 ድረስ የሦስት ሰዎች ሕይወት መቀጠፉን ነግረውናል።

ጥይቱ ከየት እንደሚመጣ አይታወቅም የሚሉት ነዋሪዎች፤ ሰዎች ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀሱና ቤተክርስቲያን ፀሎት እያደረጉ በነበረበት ወቅት በተባራሪ ጥይት ሕይወታቸው እንዳለፈ ተናግረዋል፡፡ ረቡዕ ዕለትም በጎንደር ከተማ ግብርና ምርምር ባለሙያ የሆነ አንድ ሰው በጥይት ተመትቶ ሕይወቱ ማለፉን አዲስ ማለዳ ከነዋሪዎቹ ሰምታለች።

በጎንደር ግብርና ምርምር ኢንስቲትዮት ላይ የሚሰራ አንድ ሥሙን መጥቀስ ያልፈለገ ግለሰብ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጸው፤ የግብርና ተመራማሪ የነበረው ግለሰብ በትላንትናው እለት በሽጉጥ ተመትቶ ህይወቱ እንዳለፈ ተናግሯል፡፡

ባለፈው ሚያዚያ ወር አንዲት እናትም እንዲሁ ቤተክርስቲያን በማስቀደስ ላይ እያለች በተባራሪ ጥይት ሕይወቷ እንዳለፈ ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ይናገራሉ። እንዲሁም በከተማው ውስጥ በነርስነት ሙያ ስታገለግል የነበርች ሴት ልጇን እያጠባች ባለበት ወቅት ከየት እንደመጣ ባልታወቀ ጥይት መቁሰሏንም አክለዋል።

የጦር መሳሪያ ይዘው በሚንቀሳቀሱ አካላትና ጥይት የሚተኩሱ ግለሰቦች ላይ ጥብቅ ክትትል እና ቁጥጥር ካልተካሄደ የንፁሃን ሕይወት እየጠፋ ሊቀጥል እንደሚችል ነዋሪዎቹ ጠቁመዋል፡፡

የጎንደር ከተማ አስተዳደር የጸጥታ ኮማንድ ፖስት በተለያዩ ወቅቶች የተለያዩ ክልከላዎችን እያወጣ ቢሆንም፥ ተግባራዊ ሲደረግ ግን አላየንም የሚሉት ነዋሪዎቹ ከሚያዚያ 1/2015 ጀምሮ ከተፈቀደለት የመንግሥት የጸጥታ ኃይል ውጭ የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ የተከለከለ መሆኑን አሳውቆ ነበር።

ድምፅ አልባ መሳሪያዎችን ስለታማ የሆኑ እንደ ጩቤ፣ ገጀራ፣ አንካሴ፣ ጦርና ፌሮ ብረት የመሳሰሉትን ይዞ መንቀሳቀስና በማንኛውም ቦታና ሰዓት ጥይትም ሆነ ሮኬት መተኮስ በጥብቅ የተከለከለ መሆኑን በተደጋጋሚ ክልከላዎችን ቢያወጣም ነዋሪዎቹ ተግባራዊነቱ ላይ ጥያቄ አላቸው፡፡

የፌዴራል መንግሥት እና የክልሉ መንግሥት በክልሉ በስፋት የሚንቀሳቀሰውን ራሱን “ፋኖ” ብሎ በሚጠራው ኃይል ላይ ሕግ የማስበር እርምጃ ማወጁን ተከትሎ፤ ጎንደርን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች አለመረጋጋቶች ተከስተው ከርመዋል፡፡

የመንግሥትን እርምጃ ተከትሎ በክልሉ በአንዳንድ አካባቢዎች፤ በመከላካያ እና በፋኖ ታጣዊዎች መካከል ውጊያ ሲደረግ እንደነበር አዲስ ማለዳ መዘገቧ የሚታወስ ነው፡፡

ምንም እንኳን አልፎ አልፎ የተኩስ ድምጽ መሰማት ቢቆምም አሁንም፣ በክልሉ የተፈጠረው ውጥረት አሁንም ሁነኛ መፍትሔ አላገኘም፡፡

The post በጎንደር በሚተኮስ ተባራሪ ጥይት ሰዎች እየተገደሉና እየቆሰሉ ነው ተባለ first appeared on Addis Maleda.

Source: Link to the Post

Leave a Reply