በጎንደር በሦስት ዓመታት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ 14 ዓመታትን ያስቆጠረው ግድብ ቅሬታን አስከተለ

ረቡዕ ግንቦት 2 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በአማራ ክልላዊ መንግሥት በጎንደር ከተማ አካባቢ ጠዳ ተብሎ ከሚጠራ ወንዝ ላይ እየተገነባ ያለው የመገጭ ግድብ በ 2001 በ2.4 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ወጭ ተገንብቶ በሦስት ዓመታት ውስጥ ለማጠናቀቅ የታቀደ ቢሆንም 14 ዓመታትን ማስቆጠሩ የጎንደር ከተማን ህዝብ አስቆጥቷል።

በጎንደር ከተማ አቅራቢያ በ12 ኪሎሜትር ርቀት የሚገኘው ይህ ፕሮጀክት በአገሪቱ እየተገነቡ ካሉት በርካታ ግድቦች መካከል አንዱ ሲሆን፤ ግድቡ ሲጠናቀቅ 17 ሺህ ሄክታር መሬት የማልማት አቅም ያለውና 45 ሺህ በላይ አርሶአደሮች መሬታቸውን ሦስት ጊዜ እንዲያለሙ ያደርጋቸዋል ቢባልም ለአርሶ አደሮችና ለጎንደር ህዝብ የውሃ ችግር ሊደርስ ባለመቻሉ ቅሬታን ፈጥሯል። ግድቡ ሲጠናቀቅ 185 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ እንደሚይዝ እና ከዚህ ውስጥ 116 ኪዩቢክ ሜትር ለጎንደር እና ደንቢያ ወረዳዎች ለመስኖ ልማት የሚውል ሲሆን፤ ቀሪው ለጎንደር እና አካባቢው ለመጠጥ አገልግሎት እንዲውል ታስቦ እየተገነባ ቢሆንም በግንባታ ጥራት ጉድለት የተነሳ 2013 ሃምሌ ወር ገደማ የግድቡ አንድ ጎን በውሃ መወሰዱን ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

 

በሚያዚያ ወር 2013 የመገጭ ግድብን የጎበኙት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የግንባታ ፕሮጀክቱ የአገሪቱን ሃብት በጣም ብዙ ጥቅም ላይ የዋለ ቢሆንም፤ ለመጨረስ ብዙ ጊዜ ፈጅቷል ብለዋል።

አክለውም፤ ግድቡ በቅርቡ እንዲጠናቀቅ መንግሥት ጣልቃ በመግባት አንዳንድ ማስተካከያዎችን እያደረገ እንደሆነና 70 በመቶ የሚሆነው መጠናቀቁን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በአምስት ወራት ውስጥ የመገጭ ግድብ ፕሮጀክት ተጠናቆ ለመጠጥ ውሃና መስኖ ልማት አገልግሎት እንደሚውል ገልፀው እንደነበር ይታወሳል።

ቢሆንም ግን ግድቡ ሳይጠናቀቅ 14ኛ ዓመቱን ጨርሶ ወደ አስራ አምስተኛ አመት እየተጠጋ መሆኑን አዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉ ማህበረሰቦች ተናግረዋል።

ግድቡ ከአካባቢው የመሬት አቀማመጥ ጋር ተያይዞ በክረምት ወቅት ሥራ እንደማይሰሩ የገለጹት የአካባቢው ነዋሪዎች፤ ካሁኑ ጀምረው የሥራ እንቅስቃሴያቸውን እያቆሙ መሆናቸውን አስረድተዋል። 

 

በሦስት ዓመታት ይጠናቀቃል የተባለለትን የመገጭ ግድብ ከሦስት በላይ ኮንትራክተሮች የተቀያየሩበት ሲሆን፤ በ 2013 ከ 5.9 ቢሊዮን ብር በላይ ለግንባታው ሥራ ለኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን መመደቡም ታውቋል።

አዲስ ማለዳ የመገጭ ግድብ ፕሮጀክት አማካሪ የሆኑትን ወርቅነህ አሰፋን ለማነጋገር ያደረገችው ጥረት አልተሳካም።

The post በጎንደር በሦስት ዓመታት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ 14 ዓመታትን ያስቆጠረው ግድብ ቅሬታን አስከተለ first appeared on Addis Maleda.

Source: Link to the Post

Leave a Reply