“በጎንደር ከተማ 21 ቅርሶች ለኢግዚቪሽን ይቀርባሉ” ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ታህሳስ 24 ቀን 2014 ዓ.ም… አዲስ አበባ ሸዋ የዳግማዊ…

“በጎንደር ከተማ 21 ቅርሶች ለኢግዚቪሽን ይቀርባሉ” ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ታህሳስ 24 ቀን 2014 ዓ.ም… አዲስ አበባ ሸዋ የዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ሽሩባ፣ ባህላዊ የጦር መሳሪያዎቻቸው እና ከመቅደላ የተዘረፉ ቅርሶች ዛሬ ጎንደር ከተማ ደርሰዋል። የታላቁን ንጉስ ሽሩባ አዲስ አበባ በደመቀ ሥርዓት ለጎንደር ልካለች። ጎንደርም ታላቁን ንጉስ በትልቅ ክብር ተቀብላለች። የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዘውዱ ማለደ የኢትዮጵያዊያን የጀግንነት አሻራ መለያ የሆነው ቅርስ መመለሱ የተለየ ትርጉም አለው ብለዋል። በቀጣይ ቅርሶቹ ለሕዝብ እይታ ይፋ ይደረጋሉም ብለዋል። ጥምቀትን በጎንደር ለማክበር እና ቅርሶቹን ለመጎብኘት የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል በቂ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል። በቅርቡ “በጎንደር ከተማ 21ቅርሶች ለኢግዚቪሽን ይቀርባሉ” ያሉት የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ኢትዮጵያዊያን ወደ ጎንደር በማቅናት እንዲጎበኙ ጥሪ አቅርበዋል። የቅርሶቹ መመለስ ኢትዮጵያ ካለችበት አሁናዊ ሁኔታ አንፃር የተለየ ትርጉም አለው ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር አበባው ለሀገር ውስጥ ባንዳዎች እና ለውጭ ወራሪዎች ትምህርት ይሰጣል ብለዋል። በቀጣይም የአፄ ቴዎድሮስ ሽሩባ ከእምነት አባቶች፣ ከሕዝቡ እና ምሁራን ጋር ውይይት በማድረግ በተስማሙበት ቦታ በክብር ያርፋል ተብሏል። ዘመናዊት ኢትዮጵያን ለመመሥረት፣ አዲስ ስርዓት ለማንበር እና ገናና አንድ ኢትዮጵያን ለመገንባት ርዕይ የነበራቸው ንጉስ ሽሩባ እና ቅርስ መመለሱ ለዚህ ትውልድ የተለየ ትርጉም አለው ያሉት ደግሞ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አስራት አፀደወይን (ዶክተር) ናቸው። ኢትዮጵያዊያን ለንጉሱ ያላቸውን ክብር እና ፍቅር ያክል በመርሃቸው በመጓዝ በኩል ውስንነቶች አሉብን ያሉት ዶክተር አስራት ፈለጋቸውን እና አብነታቸውን መሠረት አድርገን መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል። የንጉሡን አስተምህሮ ለማስረፅ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ አበክሮ እንደሚሰራ የገለፁት ፕሬዚዳንቱ ቀሪ ቅርሶችን ለማስመለስ ጥረት መጀመሩንም ጠቁመዋል። ቅርሶቹ ወደ ሀገር ቤት እንዲመለሱ አበርክቶ የነበራቸው ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን፣ የብሔራዊ ቅርስ አስመላሽ ኮሚቴና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በመርሐ ግብሩ ላይ ምስጋና ቀርቦላቸዋል ሲል አሚኮ ዘግቧል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply