በጦርነቱ ከወደሙ ወደ 3 ሺህ 3 መቶ ት/ቤቶች መካከል የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጣቸው 71 ት/ቤቶች ከዛሬ ጀምሮ መልሶ ግንባታቸው ሊጀመር ነው ተብሏል።
ት/ቤቶቹ 5ቱ በዲያስፖራ ፈንድ፣ 16ቱ በሰዎች ለሰዎች እና ቀሪ 50ዎቹ ደግሞ በትምህርት ሚኒስቴር ከአለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የሚሰሩ ይሆናል።
ከኢትዮጵያ ኮንትራክተሮች ማህበር ጋር በጋራ በመሆን “አዲስ የኢትዮጵያ ት/ቤቶች ዲዛይን ” በሚል እነዚህን የወደሙ ት/ቤቶች ለመስራት መወሰኑን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገልጸዋል።
የእነዚህ ት/ቤቶች ግንባታ በሶስት ምድብ ተከፍሎ ሙሉ ለሙሉ የወደሙ ፣ በከፊል የወደሙ እና ንብረቶቻቸው የተዘረፉ በሚል የሚሰራ ነው።
የመጀመሪያው በትምህርት ሚኒስቴር የሚሰራ ሲሆን ቀሪ ሁለቱ ደግሞ በክልሎቹ እና በህብረተሰብ ድጋፍ የሚሰራ ይሆናል ተብሏል።
ከወደሙት 3 ሺህ 3 መቶ ት/ቤቶች መካከል 1065 በአማራ ክልል እንዲሁም 95 ደግሞ በአፋር ክልል ይገኛሉ ያሉት የትምህርት ፕሮግራሞችና ጥራት መሻሻል
መሪ ስራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ዮሐንስ ወጋሶ ናቸው።
ከሚሰሩት 71 ት/ቤቶች መካከል በመጀመሪያው ዙር 45 ከአማራ ክልል እና 5 ከአፋር ሲሆን በዲያስፖራው ድጋፍ ከሚሰሩት መካከል ደግሞ 2ቱ ከአፋር 3ቱ ከአማራ ክልል እና ቀሪ 16ቱ ደግሞ በ 5 ክልሎች ውስጥ ሆኖ 3ቱ በአፋር እና 5ቱ ደግሞ በአማራ ክልል መሆናቸውን ስራ አስፈፃሚው ገልጸዋል።
በጦርነቱ ምክንያት 3,300 ት/ቤቶች ሙሉ ለሙሉ ሲወድሙ 4,000 ት/ቤቶች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል ተብሏል።
በእስከዳር ግርማ
ጥር 25 ቀን 2015 ዓ.ም
Source: Link to the Post