በፈረንሳይ ለጋሲዮን ወጣቶች ማዕከል ተጠልለው የሰነበቱ ተፈናቃዮች ወደ የካ ክ/ከተማ ቃኘው አደባባይ ተወሰዱ። ባህርዳር:-የካቲት 11 ቀን 2014 ዓ.ም አሻ…

በፈረንሳይ ለጋሲዮን ወጣቶች ማዕከል ተጠልለው የሰነበቱ ተፈናቃዮች ወደ የካ ክ/ከተማ ቃኘው አደባባይ ተወሰዱ። ባህርዳር:-የካቲት 11 ቀን 2014 ዓ.ም አሻራ ሚዲያ በፈረንሳይ ለጋሲዮን ወጣቶች ማዕከል ተጠልለው የሰነበቱ ተፈናቃዮች የካቲት 11 ቀን 2014 ከረፋድ ጀምሮ በመኪና ተጭነው ወደ የካ ክ/ከተማ በድሮው አጠራር ወረዳ 5 ቃኘው አደባባይ መወሰዳቸውን ለአሚማ ተናግረዋል። ከሆሮ ጉድሩ ዞን አቢ ደንጎሮ ወረዳ ከተፈናቀሉት በሽህ የሚቆጠሩ አማራዎች መካከል 320 የሚሆኑት በ3ተኛ ሻለቃ በስተጀርባ በቃኘው አደባባይ የተወሰዱ ሲሆን አዲስ አበባ ደርሰው አትገቡም ተብለው የተመለሱ እንዳሉም ተገልጧል። በፈረንሳይ የወጣቶች ማዕከል ለመግባት እና ከቤተሰቦቻቸው ጋር ያደረጉት ጥረት በፖሊሶች ክልከላ ስለገጠመው ወደ አርሲ እና አላባ የተመለሱ የወላይታ ልጆች መኖራቸውን ለማወቅ ተችሏል። አሚማ ያነጋገራቸው አቶ አለማየሁ የተባሉ አባት ከባለቤታቸው ተለይተው አትገቡም በመባላቸው መኪና በመለመን ወደ አርሲ መመለሳቸውን ከአሚማ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል። ተፈናቃዮቹ ታህሳስ 16 ቀን 2014 ከሆሮ ጉድሩ አቢ ደንጎሮ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ለ3 ቀናት ከተጠለሉ በኋላ ከተቋሟ ውጭ በመጣ ትዕዛዝ በ24 ሰዓት እንዲወጡ መደረጉና ወደ አርሲ ዞን አቦምሳ ወረዳ መርቲ ከተማ አዋሽ ጎለጎታ መድሃኒያለም መሄዳቸው ይታወሳል። በመቀጠልም የመርቲ ወረዳ የመስተዳድር አካላት ከተፈናቀላችሁበት ዞንና ወረዳ ማስረጃ ካላመጣችሁ አንቀበልም በማለታቸው የካቲት 6 እና 7/2014 ተመልሰው አዲስ አበባ ገብተዋል። በየካ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ከመግባታቸው የአዲስ አበባ ፖሊስ በሌሊት ወደ ፈረንሳይ ለጋሲዮን ወጣቶች ማዕከል ወስዷቸው ነበር። አሁን ደግሞ ለ1 ቀን ምግብና ውሃ የያዘ በጎ ፈቃደኛ ጠያቂ ጭምር አይገባም ብለው ከከለከሉ በኋላ የካቲት 11 ቀን 2014 በመኪና ጭነው በየካ ክ/ከተማ ወደ ቃኘው አደባባይ ወስደዋቸዋል። ዙሪያቸውን በፖሊስ ጥበቃ እየተደረገላቸው ሲሆን በጎ ፈቃደኞች ውሃ እና ምግብ ይዘው ወደ ቃኘው አደባባይ በመምጣት ለማገዝ ጥረት እያደረጉ መሆኑን ተጎጅዎች ተናግረዋል። የባልደራስ ፕሬዝደንት አቶ እስክንድር ነጋ እና የፓርቲው የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ቸኮል ወደ ቃኘው አደባባይ በማቅናት ተፈናቃይ ወገኖችን አነጋግረዋል፤ አጽናንተዋልም። አቶ እስክንድር ነጋ በሀገራቸው ላይ ሀገር አልባ ተደርገው እየተንከራተቱ ያሉ ወገኖችን በማየታቸው የተሰማቸውን ሀዘን በመግለጽ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች መንግስት ጥምር ኃይሉን በማስገባት ዜጎችን የመታደግ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አድርገዋል። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ኃላፊነቱን ባለመወጣቱ፣ መዋቅሩን ባለማስተካከሉ ከተጠያቂነት እንደማያመልጥም ተገልጧል። ከግድያውና ከማፈናቀሉ በስተጀርባ የክልሉ መንግስት አካላት እጅ እንዳለበትም ተፈናቃዮች አረጋግጠዋል። በወቅቱም በአካባቢው የነበሩ ፖሊሶች አታነጋግሩም፤ አትቀርጹም በማለት ወከባ ለመፍጠር ሞክረው እንዳልተሳካላቸው ለማወቅ ተችሏል። ከ320 ተፈናቃዮች መካከል ከ110 በላይ የሚሆኑት ህጻናት መሆናቸው ተገልጧል። ለፈጣንና አዳዲስ መረጃዎች የአይበገሬዎቹ ልሳን:- https://www.facebook.com/asharamedia24 ቴሌግራም :- https://t.me/asharamedia24 ለፈጣንና አዳዲስ መረጃዎች የአይበገሬዎቹ ልሳን:- https://t.me/asharamedia24 Facebook :- https://www.facebook.com/asharamedia24 ዩትዩብ:- https://bit.ly/33XmKro

Source: Link to the Post

Leave a Reply