በፌደራሉ መንግስት እና በህወሓት መካከል የሚደረገው የሰላም ንግግር በዛሬው ዕለት ተጀመረ

ማክሰኞ ጥቅምት 15 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በአፍሪካ ሕብረት አደራዳሪነት በፌደራሉ መንግስት እና በህወሓት መካከል የሚደረገው የሰላም ንግግር በዛሬው ዕለት በደቡብ አፍሪካ ተጀምሯል፡፡

ዛሬ የተጀመረው የሰላም ንግግር እስከ የፊታችን እሁድ ድረስ እንደሚዘልቅ ሮይተርስ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ስሪል ራማፎሳ ቃል አቀባይ ነግረውኛል ሲል አስነብቧል፡፡

ቃል አቀባዩ ቪንሰንት ማግዌኛ በሰሜን ኢትዮጵያ የእርስ በእርስ ጦርነት እየተፋለሙ ያሉት ኃይሎች በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር የሕብረቱ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሊሴንጉን ኦባሳንጆ፣ የቀድሞ የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እና የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ፑምዚሌ ማላምቦ-ናኩክ እንደሚያስተባብሩት ተናግረዋል።

የሰላም ንግግሩ ፍሬ እንዲያፈራ ለአስተባባሪዎቹ መልካም ምኞታቸውን የገለፁት ቃል አቀባዩ፤ “የድርድሩ ውጤት ለመላው ኢትዮጵያውያን ዘላቂ ሰላም እንዲያመጣ ደቡብ አፍሪካ ምኞቷን ትገልጻለች” ብለዋል።

ከተጀመረ ኹለት ዓመት ሊሞላው ቀናት የቀሩትን የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ለመቋጨት፤ ይህ በፕሪቶሪያ የሚካሄደው የሰላም ንግግር የመጀመሪያው ይፋዊ የንግግር መድረክ ሲሆን፤ የውይይቱ በሰላም መጠናቀቅ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምም ሆነ ለአፍሪካ ቀንድ መረጋጋት ወሳኝ መሆኑ እየተነገረ ያገኛል።

በዚህ የሰላም ንግግር ላይ ለመሳተፍም የፌደራል መንግሥት እና በህወሓት ተወካዮች ትናንት እና ከትናንት በስቲያ ወደ ደቡብ አፍሪካ ማቅናታቸው ይታወሳል።

The post በፌደራሉ መንግስት እና በህወሓት መካከል የሚደረገው የሰላም ንግግር በዛሬው ዕለት ተጀመረ first appeared on Addis Maleda.

Source: Link to the Post

Leave a Reply