በፒያሳ በቅርስነት ከተመዘገቡ 1መቶ47 ቤቶች ዉስጥ መስፈርቱን የሚያሟሉት ከ50 አይበልጡም ተባለ፡፡

በአራዳ ክ/ከተማ በ2013/14 ዓመት በቅርስነት ከተመዘገቡ 1መቶ47 ቤቶች ዉስጥ አሁን ባለዉ መስፈርት ቢመዘኑ ከ50 እንደማይበልጡ የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

በቅርስነት ከተመዘገቡት ዉስጥ አብዛኛዉ በመልሶ ግንባታ ምክንያት ለዉጦችን በማስተናገዳቸዉ እንደ ቅርስ የሚቆጠሩ አለመሆናቸዉን የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አበባዉ አያሌዉ ተናግረዋል፡፡

ብዙ ዘመን በመቆየታቸዉ ብቻ ቅርስ መሆን አለባቸዉ ተብለዉ የሚታሰቡ ህንጻዎች አሉ የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በዋናነት ቅርስ ለመባል ግን መስፈርቶችን ማሟላት አለባቸዉ ነዉ ያሉት፡፡

ከሰሞኑ በፒያሳ አከባቢ በመፍረሳቸዉ መነጋገሪያ የነበሩት የከተማ ስነ-ህንጻ ቅርሶች መስፈርቱን ባለማሟላታቸዉ የፈረሱ ናቸዉ ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ከ2014 ጀምሮ የከተማ ስነ-ህንጻ ቅርስ መመሪያ ወጥቶ እየተሰራበት መሆኑን ገልጸዉ ፤ በአራዳ ክፍለ ከተማ ከተመዘገቡት 1መቶ47 ቤቶች መካከል በዚህኛዉ መመሪያ መስፈርቱን የሚያሟሉት ጥቂቶች ብቻ ናቸዉ ብለዋል፡፡

ቅርስ ሁሌም ቢጠበቅ መልካም ነዉ ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ከልማት ጋር እንዴት ይጣጣም የሚለዉን ነዉ መመልከት ያለብን ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ልማት የተወሰነ ቅርስን ይጎዳል ይህ የትም ያለ ጉዳይ ነዉ ሲሉ የሚጨምሩት ዋና ዳይሬክተሩ ፤ 90 ዓመት የቆየ ህንጻን ላለማንሳት ስንል 200ሺህ ሰዉ የሚጠቅም ልማት ማቆም አንችልም ሲሉ ገልጸዋል፡፡

እንደ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ከሆነ አንድ ህንጻ ቅርስ ነዉ ለመባል አምስት መስፈርቶችን ማሟላት አለበት የተባለ ሲሆን፤ ይህም ስነ-ህንጻዉ፣ታሪኩ፣ ከባቢያዊ ነገር፣የሚሰጠዉ አገልግሎት እና አሁናዊ ሁኔታ የሚሉት ናቸዉ፡፡

እስከዳር ግርማ

መጋቢት 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply