በፖለቲከኛው በቴ ኡርጌሳ ግድያ ዙሪያ “አሳፋሪ” ምርመራ እየተደረገ ነው፤ የዓይን እማኞች የደረሱበት አልታወቀም- ኦነግ 

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የድርጅቱ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ የነበሩት በቴ ኡርጌሳ ግድያን በተመለከተ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን “አሳፋሪ” የምርመራ ሂደት እየተከተለ ነው ሲል ወቀሰ። 

በቴ ኡርጌሳ ከእንግዳ ማረፊያው ሲወሰድ የተመለከቱ አንድ የጥበቃ ሰራተኛ ከክስተቱ በኋላ የገቡበት እንዳልታወቀ ኦነግ በመግለጫው አመልክቷል።

ኦነግ የአባሉን ግድያ የተመለከቱ ጉዳዮችን እየተከታተለ መሆኑን ባሳወቀበት እና ትላንት ባሰራጨው መግለጫ፤ ግንባሩ በመንግስት በኩል የሚደረገው “ምርመራ ተብየው” ለሂደቱ ተዓማኒነት መጓደል ምክንያት የሚሆኑ ገለልተኛነት ያልሆኑ ማስረጃዎች መኖር፣ ማስረጃዎች መደምሰስ እንዲሁም የሀሰት መረጃዎች መኖርን ጠቁሟል። 

ስለዚህም በባቲ ኡርጌሳ ግድያ ላይ የሚደረገው ምርመራ እየተባለ የሚጠራው መረጃ ከጅምሩ ሆን ተብሎ በተዘበራረቁ በርካታ የማስረጃዎች፣ የተሳሳቱ መረጃዎች እና የሀሰት ዘመቻዎች የተበላሸ መሆኑን ደግመን እንገልፃለን። አጠቃላይ የሚታየው ሁኔታና የመንግስት የጸጥታ አካላት ባህሪ “በደርግ ጊዜ እና ቀይ ሽብር” ወቅትን ይመስላሉ ሲል ኦነግ ገልጿል።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ የሆኑ በቴ ኡርጌሳ በትውልድ ስፍራቸው በኦሮሚያ ክልል መቂ ከተማ ማክሰኞ ሚያዝያ 1 ቀን 2016 ለረቡዕ አጥቢያ መገደላቸው አይዘነጋም። ኦነግ የበቴ ኡርጌሳን ግድያ በተመለከተ በማስረጃ አረጋግጫለሁ ያላቸውን ጉዳዮች በዝርዝር አስታውቋል። በዚህም መግለጫው በወጣበት ሚያዝያ 6 ቀን 2016 እንደገለጸው 

  1. በቴ ኡርጌሳ ‘አበበ ጊራዝማ’ ከተባለ የእንግዳ ማረፊያ ክፍላቸው በመንግስት የደህንነት አካላት መወሰዱን  
  2. ከማረፊያ ክፍሉ ውስጥ እየጎተቱ የወሰዱት የደህንነት ሰዎች ከፍተኛ ድብደባ የፈጸሙበት ሲሆን በሕግ አግባብ እንዲይዙት መማጸኑ
  3. ድርጊቱን የተመለከተው የእንግዳ ማረፊያው ጠባቂ/ዘበኛ ማስረጃ ለመደበቅ ታፍኗል/ተሰውሯል አልያም መገደሉ
  4. ወታደራዊ ዩኒፎርም የለበሱ የደህንነት አባላት በቴ ኡርጌሳን በተሽከርካሪ ላይ ከጫኑ በኋላ ወደ ቆሻሻ ቦታ በመውሰድ ጎትተው ካወረዱ በኋላ እጆቹን በጀርባው አስረው በመጨረሻም በጥይት ተኩሰው እንደገደሉት የአካባቢው ነዋሪዎች አይተዋል። አስክሬኑን በአውሬ ከመበላት ለመጠበቅ በቦታው የነበሩ የአካባቢው ሰዎች በኃይል ጠፍተዋል ወይም መገደላቸው
  5. ከክልሉ መንግስት እና ከብልፅግና ፓርቲ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው ቡድኖች ወይም ግለሰቦች ግድያውን ከቤተሰብ ጋር ለማያያዝ በተሳሳተ መንገድ እየሰሩ ስለመሆኑ 
  6. ባለፉት አምስት ዓመታት ሰላማዊ የፖለቲካ፣ የባህልና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ላይ የተፈጸሙት የግድያ አሠራርና ‘ምርመራ’ እየተባለ የሚጠራው አካሄድ የፍትህ እጦት የተፈፀመበት በመሆኑ በመንግስት በኩል የሚደረገው ምርመራ ምንም ዓይነት ገለልተኛ የመሆን ዕድል እንደሌለው አረጋግጫለሁ ሲል ኦነግ አስታውቋል።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ሂዩማን ራይትስ ዎች፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና የአፍሪካ ሕብረት አካላት እንዲሁም የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቦችና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ገለልተኛ እና ከፓርቲ የጸዳ ምርመራ እንዲያደርጉ ጠይቋል።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በበኩሉ በግድያው ማግስት ባወጣው መግለጫ የተሟላ ምርመራ ተደርጎ ጥፋተኞች ሳይታወቁ የፖለቲካ አቋም ልዩነት በመኖሩ ብቻ ወደመንግስትም ሆነ ሌላ አካል የሚጠቆሙ ጣቶች አግባብ አይደሉም በማለት ግድያውንም እንደሚያወግዝ በመግለጫ አስታውቆ ነበር። ነጻና ገለልተኛ ምርመራ እንደሚደረግም ቃል ገብቶ ነበር።

Source: Link to the Post

Leave a Reply