”በ100 ሺህ የሚቆጠር ታጣቂ ሰብስቦ የሚቀልብ አካል ስለ ትግራይ ህዝብ ረሃብ የማውራት ሞራል የለውም“ -መንግስት-

የትግራይ  ክልል በመላው ኢትዮጵያ እጅግ  ከፍተኛ ጉዳት ካስከተለውና  በደርግ ዘመነ መንግስት ከተከሰተው የ1977ቱ ረሃብ የከፋ አደጋ ውስጥ ለመግባት ጫፍ ላይ መድረሱን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ባወጣው መግለጫ፤ 90 በመቶ የሚሆነው  የክልሉ ነዋሪ ህዝብ ለከፋ ረሀብና  ለሞት ተጋላጭ መሆኑን አመልክቷል።
በትግራይ የነበረው አውዳሚ የጦርነት አሻራና ድርቅ ያስከተለው ረሀብ አደገኛ ጥምረት መፍጠራቸውን የጠቆመው የጊዜያዊ አስተዳደሩ  መግለጫ፤  የፌደራል መንግስቱና አለም አቀፍ ተቋማት እያንዣበበ ያለውን  የረሀብና የሞት አደጋ ለማስቀረት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቋል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ በዚህ መግለጫው፤በጦርነቱ ወቅት የትግራይ የኢኮኖሚ መሰረት መድቀቅ፣ የጤና ተቋማት መውደምና ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆነው የክልሉ  ህዝብ መፈናቀል፣ በትግራይ ብዙዎች ድህነትን መቋቋም እንዳይችሉ አድርጓቸዋል ሲል ገልጿል። ከዚህ በተጨማሪም   የዝናብ እጥረት፣ የአንበጣ መንጋ መከሰትና የሰብአዊ እርዳታ መቋረጥ በክልሉ ያለውን ችግር አባብሶታል ብሏል ።  ይህንን በክልሉ ተከስቷል የተባለውን የረሃብ  አደጋ ለመቋቋም የሚያስችል  የገንዘብ አቅም  እንደሌለው የገለጸው  ጊዜያዊ አስተዳደሩ፤ የፌደራል መንግስትና አለም አቀፍ ተቋማት በክልሉ የተከሰተውን የረሀብና የሞት አደጋ ለማስቀረትና ለነዋሪው ሕዝብ ችግር መፍትሔ ለመስጠት  መስራት እንደሚገባቸው ገልጿል። አያይዞም፤  ችግሩ የማይፈታ ከሆነ  ሀገራዊና ቀጣናዊ ሰላምና መረጋጋትን ሊያውክ እንደሚችል አስታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ ይኸው በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የተሰጠውና  ክልሉ ከ1977ቱ ጋር የሚስተካከል ድርቅና ረሃብ ቀውስ  ውስጥ  ሊገባ ጫፍ ላይ መድረሱን  የሚጠቁመው መግለጫ፤  ፈጽሞ ስህተት  መሆኑን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት አስታወቋል።
የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ  ዶ/ር ለገሰ ቱሉ    በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት መግለጫ  እንዳስታወቁት፤ በአገር ደረጃ እንዲህ አይነት ቀውስ ሲኖር መታወጅ ያለበት በፌደራል መንግስት በኩል የፌደራል የአደጋ ስጋት አመራር ምክር ቤት በኩል  ነው ያሉት ዶ/ር ለገሰ፤ ይህም ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን ማእከል በማድረግ ተገምግሞ  ነው ብለዋል ። የፌደራል የአደጋ ስጋት አመራር ምክር ቤት በትግራይ ክልል አራት ዞኖች ድርቅ መከሰቱን ቢያረጋግጥም፣ ከ77ቱ ድርቅና ረሃብ ጋር ይስተካከላል የሚል መረጃ እስካሁን እንዳላወጣም ሚኒስትሩ  ጨምረው ገልጸዋል።
ዓለም አቀፋ አጋር አካላት እርዳታ ባቆሙበት ሰዓት  መንግስት ፕሮጄክቶቹን ሁሉ  አጥፎ ለትግራይ ክልል በበቂ ሁኔታ እርዳታ እያቀረበ እንደነበር ያስታወሱት ሚኒስትሩ፤ በ100 ሺህ የሚቆጠር ታጣቂዎችን በባለሙያ ስም በአንድ ቦታ ሰብስቦ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በተመደበ በጀት እየቀለቡ፣ በምን ሞራል ነው ስለ ትግራይ ህዝብ ረሐብና ስቃይ ማውራት የሚቻለው?” ሲሉም ጠይቀዋል። በህዝብ ሽፋን የሚደረግ የትኛውም አይነት ፕሮፓጋንዳ ተቀባይነት እንደማይኖረውም ገልጸዋል ።

Source: Link to the Post

Leave a Reply