በ2017 በአገር አቀፍ የፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂ ተግባራዊ ይደረጋል ተባለ 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በአገር አቀፍ ደረጃ የቀረጸው የፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂ በክልል  ደረጃ ተግባራዊ እንደሚሆን ኤፍኤስዲ (FSD) ኢትዮጵያ አስታወቀ። 

ትላንት መጋቢት 5 ቀን 2016 ፖሊሲ አውጪዎች፣ ባለሙያዎች፣ የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች፣ ተቆጣጣሪዎች፣ የልማት ድርጅቶች እና የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በተገኙበት ‘በአፍሪካ የሴቶች የፋይናንስ አካታችነት መሰናክሎችና ዕድሎች’ በሚል ርዕስ ጉባዔ ተካሄዷል። 

በኤፍኤስዲ ኢትዮጵያ የፋይናንስ አካታችነት ዳይሬክተር አቤል ታደለ የፋይናንስ አካታችነት በየተለያዩ አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችለውን ክልላዊ ስትራቴጂ ከብሔራዊ ባንክ ጋር በመተባበር በመጪው የበጀት ዓመት በክልሎች ወደ ተግባር እንደሚገባ ገልጸዋል።

በጉባዔው የሴቶችን የፋይናንስ ተደራሽነት እና አጠቃቀምን ለማስፋት በሚቻልባቸው ስልቶች ላይ ውይይት ተካሄዷል። በተጨማሪም የዓለም ባንክ በየሁለት ዓመቱ የሚያወጣውን መረጃ ተመርኩዞ በአምስት የአፍሪካ አገራት ላይ የተሰራ ጥናት ገለጻ የተደረገ ሲሆን፤ በጥናቱ ሴቶች በኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት አገልግሎትን እንዳይጠቀሙ ያደረጓቸው ተግዳሮቶች ቀርበዋል።

ሴቶች ያላቸው የትምህርት ደረጃ፣ የሚቆጥቡት ገንዘብ አለመኖር እንዲሁም በአካባቢያቸው የፋይናንስ ተቋማት ተደራሽ አለመሆን ሴቶች በፋይናንስ ውስጥ ላለመካተታቸው ዋነኛ ምክንያት መሆናቸውን አዲስ ማለዳ ከጉባዔው ሰምታለች። 

ፋይናንስ አካታችነት ዳይሬክተሩ አቤል በተለይ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፤ “የፋይናንስ አካታችነት ትግበራ ላይ ተቋማት ከሚሰሩት ስህተተ አንዱ ለሁሉም ሴቶች ተመሳሳይ አገልግሎት ለመስጠት መሞከራቸው ነው”።

የፋይናንስ ተቋማት በመልከ ብዙ ዘርፎች ሴቶችን ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸው ያሳሰቡት የኤፋኤስዲ ዳይሬክተር፤ የገቢ ምንጭ የሌላትን ሴት ደግሞ የገቢ ምንጭ እንዲኖራት በማድረግ የፋይናንስ አካታችነት እንደሚጀምር አጽንዖት ሰጥተዋል። 

በተመሳሳይም የፋይናንስ ተቋማት አማራጮችን በማስፋት እንዲሁም እነዚህ ተቋማት “ለባለሀብቶች ብቻ ነው” ብለው የሚያስቡ ሴቶች ወደ ስርዓቱ ማካተት መቻል አስፈላጊ መሆኑ ተመላክቷል። የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነትን ከማስፋት አንጻር የተሻለ ተግባር መኖሩም ተጠቁሟል።

ሴቶችን በፍትሃዊነት ሳያካትት የፋይናንስ አካታችነትን እውን ማድረግ አይቻልም” የሚሉት ዳይሬክተሩ “ሆኖም ጥናቱ በግልፅ እንደሚያሳየው ኢትዮጵያ እንደሌሎች አገራት በፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነትና አጠቃቀም ላይ የሚታየውን የሥርዓተፆታ ክፍተት ለመሙላት አሁንም ትልቅ ስራ ይጠብቃታልሲሉ አክለው ገልጸዋል።  

Source: Link to the Post

Leave a Reply