በ23ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለተካፈለው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ የልዑካን ቡድን የእውቅናና የሽልማት መርሃ ግብር ተደረገ፡፡

ዛሬ በግዮን ሆቴል በ23ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ተካፍሎ በ5 ወርቅ፣ በ4ብር እና 1ነሃስ በአጠቃላይ በ10 ሜዳልያዎች በማግኘት ከደቡብ አፍሪካ፣ ኬንያንና ናይጄሪያን ተከትሎ 4ኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን ላጠናቀቀው የልዑካን ቡድን የማበረታቻ እና የእውቅና መርሃግብር የተካሄደ ሲሆን በዚህ መሠረት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን 1,305,000.00 ብር ለማበረታታት የመደበ ሲሆን ለቡድን መሪዎች፣ ለቴክኒክ ቡድን መሪዎች፣ ሜዳሊያና ዲፕሎማ ላስገኙ አትሌቶች፣ ለተሳተፉ አትሌቶች፣ ለአሰልጣኞች እና ለልዑካን ቡድን አባላት እንደየ ደረጃቸው የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቷል።

ወ/ሮ ፎዚያ ኢድሪስ የቡድኑ መሪ እና አቶ አሰፋ በቀለ የቴክኒክ ቡድን መሪ ስለነበራቸው ቆይታቸው አጠቃላይ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን በተጨማሪ ድጋፍ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

አትሌቶችን በመወከል አትሌት ስንታየሁ ማስሬ እና አትሌት ንብረት መልአክ በካሜሮን ስለነበራቸው የውድድር ቆይታቸው የተናገሩ ሲሆን ፤ አሰልጠኞችን በመወከል አሰልጣኝ ጌታሁን ታደሰ የነበራቸው ቆይታ አጠቃላይ ማብራርያ በመስጠት ፌዴሬሽኑ ወደፊት ትኩረት ተሰጥቶት መሥራት የሚገባውን አመላክቷል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ክብርት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ ባስተላለፉት መልእክት:- በ23ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለተገኘው ውጤት መሳካት የአገርን ጥሪ ተቀብላችሁ ለተሳተፋችሁ አትሌቶች እና ከፌዴሬሽኑ ጋር በጋራ በመሆን ለሰሩና ላገዙ አካላት በፌዴሬሽኑ ስም ምስጋና በማቅረብ ለፖሪስ 2024 ኦሎምፒክ ለአትሌቶቻችን መልካም እድል ተመኝተዋል።

የኢትዮጵያን አትሌቲክስ ደጋፊዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ምንያህል ጌታቸው ሁልጊዜ ውድድር ሳንመርጥ የአትሌቲክስ ዉድድሮችን እንደሚደግፊ ተናግረዋል።

በዚህ መርሀግብር ላይ የካሜሮን ኤምባሲ ተወካይ ዊያንግ ላዋ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ፣ የኢ.አ.ፌ አቃቤ ንዋይ አቶ ተፈራ ሞላ ፣ የኢ.አ.ፌ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ረዳት ኮሚሽነር ማርቆስ ገነቲ ፣ የኢ.አ.ፌ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ዶ/ር ተስፋዬ አስገዶም ፣ የኢ.አ.ፌ ም/ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ማስተዋል ዋለልኝ ታዋቂ አትሌቶችና አሰልጣኞች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና የኢትዮጵያን አትሌቲክስ ደጋፊዎች ማህበር ተገኝተዋል።

(EAF)
ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ሰኔ 21 ቀን 2016 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply