በ38 ዓመታት የሚከፈል 207.2 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የብድር ጥያቄ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተላለፈ

ዓርብ ሰኔ 07 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) ዛሬ በተካሄደው 35ኛ መደበኛ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ በ207.2 ሚልየን ዶልር ብድር ላይ እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ውሳኔ አሳልፏል።

የኢትዮጵያ መንግስት ከዓለም አቀፍ የልማት ማህበር ጋር የ2ኛ ዙር የከተሞች የመጠጥ ውሃ አቅርቦት እና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የሚውል 207 ሚልየን 200 ሺህ ዶላር ብድር ለማግኘት የተፈረመውን ስምምነት እንዲጸድቅ በሙሉ ድምጽ ለፓርላማው አስተላልፏል።

ብድሩ ወለድ የማይታሰብበት፣ 0.75 በመቶ የአገልግሎት ክፍያ የሚከፈልበት እና 6 ዓመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ38 ዓመት ተከፍሎ የሚጠናቀቅ ሲሆን ብድሩ ከአገሪቱ የብድር አስተዳደር ፖሊሲ ጋር የሚጣጣም ነው ተብሏል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የንብረት ታክስ ረቂቅ አዋጅ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ረቂቅ አዋጅ፣ ስለባንክ ስራ የቀረበ ረቂቅ አዋጅ እንዲሁም የአካባቢና ማህበራዊ ተጽዕኖ ግምገማ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ በሙሉ ድምጽ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስተላልፏል።

እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ረቂቅ አዋጅ ላይ ሲሆን የንግድ ባንክን የፋይናንስ አቅርቦት እና አቅም ላማሻሻል በቀረቡ ሀሳቦች ላይ ተወያይቶ ወደቀጣይ ተግባር እንዲገቡ ወስኗል፡፡

የብሔራዊ ባንክ ረቂቅ አዋጅ ከገንዘብ ፖሊሲ ውጤታማነት እንዲሁም በፋይናንስ ራስን ከመቻል አንጻር ክፍተቶች ያሉበት በመሆኑ፤ ባለፉት ዓመታት በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰቱ በርካታ የኢኮኖሚ፣ የፋይናንስ፣ የቴክኖሎጂና የጂኦ-ፖለቲካ ለውጦች በመኖራቸው፤ አዋጁን ማሻሻል እንደሚገባ ስለታመነበት ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቷል ተብሏል።

ስለባንክ ስራ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ለረጅም ጊዜ ዝግ የነበረው የባንክ ስራን ለውጭ አገራት ክፍት ማድረጓን ተከትሎ ይህንን ለመምራት፣ የፈቃድ አሰጣጥን ለመወሰን እና ለማስተዳደር የሚያስችል የሕግ እና የቁጥጥር ስርዓት መዘርጋት የሚያስችል ነው።

Source: Link to the Post

Leave a Reply