በ4 ወራት ይፈጸማል የተባለው የላዳ ታክሲዎች ቅያሬ ከ4 ዓመታት በላይ አስቆጠረ

መንግስት የላዳ ታክሲዎችን ለደህንነት እና ለከተማ ገጽታ ሲል በአዲስ ተሽከርካሪዎች እንዲተኩ እንቅስቃሴ ከተጀመረ ዓመታት ቢቆጠሩም አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የላዳ ታክሲ ባለንብረቶች “በወራት ውስጥ ትረከባላችው የተባልነው መኪና እጃችን ሳይገባ ዓመታትን እያስቆጠርን ነው” ሲሉ የሚያሰሙት አቤቱታ ሰሚ ማጣቱን አስረድተዋል።

መኪኖቻችን አሮጌ እና ጥገና፣ መለዋወጫና መሰል አገልግሎቶች (በተለምዶ ሰርቪስ) በአግባቡ ባለማግኘታቸው እንዲሁም ተወዳዳሪ የሜትር ታክሲ አገልግሎት ሰጪዎች በመበራከታቸው ተመራጭነታቸው ቀንሷል። በዚህም ገቢያቸው መቀዛቀዙንና ስራ መስራት እንዳልቻሉ ቅሬታቸውን ለሚዲያችን ገልጸዋል።

የላዳ አገልግሎት ሰጪ አሽከርካሪዎች 20 በመቶ ቅድሚያ ክፍያ ከባንክ ጋር በማገናኘት ክፍያውን ከፈጸሙ በኋላ አዲስ ታክሲ እንደሚሰጣቸው እና 80 በመቶውን በየወሩ እየሠሩ ከሚያገኙት ገቢ ላይ እንደሚከፍሉ ተነግሯቸው ከአራት ዓመታት በፊት ከኤል አውቶ ኢንጂነሪንግና ትሬዲንግ ጋር ተፈራርመዋል።

የታዘዙትን 20 በመቶ ቅድመ ክፍያ ቢፈጽሙም ተግባራዊ የተደረገ ነገር የለም ማለታቸውን አዲስ ማለዳ መዘገቧ ይታወቃል።

አዲስ ማለዳ ከተለያዩ የላዳ ማህበራት ባገኘችው መረጃ ኤል አውቶ የተባለው ድርጅት ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት 240 መኪኖችን አስመጥቶ ለ40 ማህበራት ለእያንዳንዳቸው 6 መኪኖችን ብቻ አከፋፍሎ የውዝግብ መነሻ ሆኖ እንደነበር ባለንብረቶቹ ያስታውሳሉ። ይሁን እንጂ በአዲስ አበባ ከተማ እያንዳንዳቸው ከ30 እስከ 40 እና ከዚያ በላይ አባላት ያላቸው ከ200 የሚበልጡ የላዳ ማህበራትይገኛሉ። 

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ በአንድ የላዳ ባለንብረቶች ማህበር ውስጥ ኮሚቴ የሆኑ ግለሰብ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት “ችግሩ ያለው አስመጪው ድርጅት ጋር ነው፤ በየጊዜው የተለያየ ምክንያት እየሰጡ ነው የሚያጓትቱት”።

በተጨማሪም ድርጅቱ 540 መኪኖችን እንዳስገባ ያሳወቀ ቢሆንም አንድ ጊዜ ባንኮች በውላቸው መሰረት 80 በመቶ ክፍያውን እያደረጉ አይደለም በማለት፤ በሌላ ቀን ደግሞ ተገጣጥመው አላለቁም የሚል ምክንያት በመስጠት እስካሁን ተጠቃሚው ጋር እንዳልደረሰ አባላቱ ጠቁመዋል።

የላዳ አገልግሎት ሰጪዎች መሸጥ መለወጥ እንዲሁም ደግሞ ከዘመናዊ መኪና ባለቤቶች ጋር ተወዳዳሪ ሆኖ መስራት አለመቻላቸው ለከባድ የኑሮ ቀውስ እንደዳረጋቸው ተናግረዋል። 

“ከዛሬ ነገ ይሰጠናል በማለት እየጠበቅን ቢሆንም አቤቱታችንን እና ቅሬታችንን የሚሰማን አጥተናል፤ ከኛ አልፎ ቤተሰቦቻችንን ማስተዳደር ተቸግረናል፤ መንግስት ጉዳዩን መፍትሄ ይስጥልን” ሲሉም አሳስበዋል።

ተሸከርካሪዎቹ በአዲስ እንዲተኩ መደረጉ ባለንብረቶቹን በተሸከርካሪዎቹ እርጅና ሳቢያ ከሚደርስባቸው ከፍተኛ የነዳጅና የመለዋወጫ ወጪ ለማዳን፣ በገበያ ላይ ተወዳዳሪ ሆነው በመስራት ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ፣ የአከባቢ ብክለትን ለመቀነስ እንዲሁም የከተማዋን ገፅታ ለማሻሻል ተብሎ ቢጀመርም በታሰበለት አቅጣጫ አለመሄዱ ባለንብረቶቹን ለከፋ ችግር ዳርጓል። 

ይህ በእንዲህ እንዳለ በለፈው ወር ታህሳስ 18 ቀን 2016 የላዳ ታክሲዎችን በአዲስ ለመተካት የሚደረገውን “ጥረት ለደገፉ አካላት ምስጋና የማቅረብ መርሃ ግብር” የተባለ መድረክ በወዳጅነት ፓርክ ተካሂዷል። በመርሃ ግብሩ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትና የገንዘብ ሚኒስቴርን ጨምሮ አሮጌ የላዳ ታክሲዎች በአዲስ ለመተካት የተደረገውን ጥረት ለደገፉ አካላት ምስጋና መቅረቡን ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዘግቦ ነበር።

ከተያዘው እቅድ እና ፕሮጀክቱ ከተጀመረመባቸው ምክንያቶች አንዳቸውም ሳይሳኩና ውጤታቸው ሳይመዘን እና በተገቢው መንገድ ሳይረጋገጥ እውቅናም ሆነ ምስጋና የመቅረቡ አግባብነትን አዲስ ማለዳ ትጠይቃለች። 

ታከለ ኡማ የአዲስ አበባ ከንቲባ በነበሩበት ጊዜ የላዳ ታክሲ ባለቤቶች ተደራጅተው እንዲቀየሩ ተብሎ  የወጣውን ጨረታ ኤል አውቶ ኢንጂነሪንግ አሸንፎ በአንድ ዓመት 10 ሺህ 500 ማለትም በየ4 ወሩ 3000 መኪኖችን አስገብቼ እጨርሳለሁ የሚል ውል ሠጥቶ ማፈራረሙ አይዘነጋም።

አዲስ ማለዳ የኤል አውቶ ድርጅት ምላሽን ለማካተት ያደረገችው ተደጋጋሚ ጥረት ስልክ ባለመመለሳቸው ይህ ዘገባ እስወጣበት ሰዓት ድረስ ያልተሳካ ሲሆን ምላሻቸውን ለማስተናገድ አዲስ ማለዳ በማንኛውም ጊዜ ዝግጁ ናት።

Source: Link to the Post

Leave a Reply