በ8.5 ቢሊዮን ብር 600 አፓርታማዎች ሊገነቡ ነው

በ8.5 ቢሊዮን ብር 600 አፓርታማዎች ሊገነቡ ነው

በሁለት ዓመት ውስጥ የጠናቀቃሉ ተብሏል
                      
        በቤቶች ልማት ዘርፍ ላይ የተሰማራው “ኤን ኤም ሲ (NMC) ሪል እስቴት በሀገሪቱ ያለውን የቤት እጥረት ለመቀነስና ለማቃለል በ8 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር  ካፒታል 600 አፓርታማዎችን ሊገነባ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታውቋል። በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 ልዩ ስሙ ቱሉ ዲምቱ አደባባይ ፊት ለፊት በሚገኘው ቦታ ላይ የሚገነቡት አፓርማዎች ዘመናዊና ለኑሮ ምቹ አንደሚሆኑ ተጠቁሟል። በዚሁ ፕሮጀክት ባለ ሁለት ወለል 30 ቪላዎችና 14 ብሎክ ያላቸው ባለ 12 ወለል አፓርታማዎችም ደረጃቸወን ጠብቀው እንደሚገነቡ በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ እንደሚጠናቀቁም ለማወቅ ተችሏል።
በ35 ሺህ ካሬ ሜት ላይ ያረፈውና በ2017 ዓ.ም (ከሁለት ዓመት በኋላ) ተጠናቅቆ ለነዋሪዎች ይተላለፋል በተባለው በዚህ ፕሮጀክት ግንባታ የቻይናና የህንድ የምህንድስና ባለሙያዎች ይሳተፉበታል የተባለ ሲሆን፤  የዚሁ ስምምነት የፊርማ ስነ-ስርዓት ዛሬ ከረፋዱ 5፡00 ጀምሮ አትላስ አካባቢ በሚገኘው ቤዝ ኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ሆቴል እንደሚካሄድ፤ የሥነ-ስርዓቱ አስተባባሪ ተወዳጅ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ለአዲስ አድማስ በላከው መግለጫ አስውቋል። ፕሮከጀክቱ በኢትዮጵያ በተለይ በአዲስ አበባ ያጋጠመውን ከፍተኛ የመኖሪያ ቤት እጥረት ከማቃለሉም ባሻገር ለ2 ሺህ 300 ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጥር የተገለጸ ሲሆን፤ ፕሮጀክቱ አሁን በጅምር ላይ ሆኖም ለ400 ሰዎች የስራ እድል ፈጥሯል ተብሏል። በአሁኑ ሰዓት በዚህ ፕሮጀክት ሳይት ላይ የከርሰ ምድር ውሃ ከመውጣቱም በላይ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ተሰርተው ያለቁ ሲሆን የግንባታ ሰራተኞች መኖሪያም በሳይቱ ላይ ተሰርቶ ሰራተኞች በትራንስፖረት ችግር የሚያባክኑትን ሰዓትና ጉልበት ማዳን ተችሏል ተብሏል፡፡ የአፓርታማዎቹ ግንባታም በ2017 ዓ.ም ግንቦት ወር ላይ ሙሉ ለሙሉ ለነዋሪዎች እንደሚተላለፉም ታውቋል።
በኢትዮጵያዊው ባለሀብት በአቶ መሰረት መኮንን ባለቤትነት በሚመራው በዚህ ፕሮጀክት ማስጀመሪያ ሥነ-ስርዓት ላይ ራሳቸውን ባለሀብቱን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ በሪል እስቴት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎችና ባለሃብቶች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደሚታደሙ የተወዳጅ ሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ዋና ስራ አስኪያጅ ጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ ገልጿል።
ኤን ኤም ሲ ሪል እስቴት በሀገሪቱ ያለውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለማቃለል በክልል ከተሞችም የቤት ልማት ስራዎችን የማከናወን እቅድ ነድፎ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ለማወቅ ተናግሯል።  

Source: Link to the Post

Leave a Reply