“ቢያንስ ከ45 በላይ ሲቪል ሰዎች” በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ተገድለዋል- ኢሰመኮ

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአማራ ክልል በሰሜን ጎጃም ዞን በመራዊ ከተማ ጥር 20 ቀን 2016 በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በታጠቁ ኃይሎች (ፋኖ) መካከል ከጠዋቱ 12 ሰዓት አካባቢ ጀምሮ ውጊያ መካሄዱን ተከትሎ በሲቪል ሰዎች ላይ የደረሰው ጉዳት እየተመረመረ መሆኑን አስታውቋል። 

ኮሚሽኑ ዛሬ ባወጣው መግለጫ “ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት የጠየቃቸው መረጃዎች እና ምላሽ ገና ያልደረሰ” መሆኑን እና “የተሟላ ምርመራ መደረጉ አስፈላጊነት” ገልጾ፤ እስካሁን ድረስ በተደረገው ክትትል ማንነታቸው የተረጋገጠ ቢያንስ 45 ሲቪል ሰዎችን የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች “ለፋኖ ድጋፍ አድርጋችኋል” በሚል ምክንያት ከሕግ ውጭ ገድለዋል ብሏል። 

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ “በዚህ ግጭት በሁሉም ወገኖች በተለይም በየአካባቢው ነዋሪዎችና በሲቪል ሰዎች ላይ እየደረሰ ያለው ሥቃይ እጅግ እየጨመረ በመምጣቱ ሁሉም ወገኖች ብቸኛው ዘላቂ መፍትሔ ሠላማዊ ውይይት መሆኑን ተቀብለው በቁርጠኝነት ይተገብሩት ዘንድ፣ እንዲሁም የተሟላ ምርመራ ተደርጎ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ እና የተበደሉም እንዲካሱ አሁንም በድጋሚ ጥሪያችንን እናቀርባለን” ሲሉ አሳስበዋል። 

በተጨማሪም “የፋኖ አባላት ናቸው” በሚል ተጠርጥረው የተያዙ እና ለጊዜው ብዛታቸውን ለማረጋገጥ ያልተቻለ ሰዎች በተመሳሳይ ሁኔታ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ከሕግ ውጭ መገደላቸውን ኢሰመኮ ገልጿል። 

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ከጥቆማዎችና ከልዩ ልዩ መረጃ ምንጮች ከተሰበሰቡት የሲቪል ሰዎች ስም ዝርዝር ውስጥ የ45ቱ መሞት ቢረጋገጥም፤ “ነገር ግን የጉዳቱ መጠን ከዚህ ሊበልጥ እንደሚችል ምክንያታዊ ግምት ለመውሰድ ተችሏል” ሲል አስታውቋል። 

ኢሰመኮ ከምስክሮች ባገኘው መረጃ መሠረት “ለቀን ሥራ በጠዋት ከቤታቸው ወጥተው ድንገት ተኩስ ሲከፈት በአንድ ቦታ ተጠልለው የነበሩ 18 ሲቪል ሰዎች የተገደሉ መሆኑን፣ ቀበሌ 02 አካባቢ በተለምዶ ሚሊኒየም ተብሎ በሚጠራ ሰፈር አንድ የጠፋ አባልን ሲያፈላልጉ የነበሩ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች “በፍለጋው አልተባበሩም” ያሏቸውን 8 ሲቪል ሰዎችን መግደላቸውን እንዲሁም 12 ባጃጆች በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች መቃጠላቸው” ተገልጿል። 

የመብቶች ኮሚሽኑ በአማራ ክልል በአጠቃላይ የግጭት ዐውድ በሲቪል ሰዎች ላይ የሚደርስ ጉዳት፣ በታጣቂ ቡድኖች በሚፈጸሙ ጥቃቶች የሚደርሱ ጉዳቶች፣ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በሲቪል ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ከሕግ ውጭ ግድያዎች አሁንም እጅግ አሳሳቢ ሆነው ቀጥለዋል ብሏል።  

በሌላ በኩል በምሥራቅ ጎጃም ዞን ሸበል በረንታ ወረዳ የዕድውኃ ከተማ ጥር 10 ቀን 2016 በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በተካሄደ የተኩስ ልውውጥ ታጣቂዎች ከተማዋን ለቀው ከወጡ በኋላ ቤት ለቤት በተደረገ ፍተሻ፣ እንዲሁም መንገድ ላይ የተገኙ ቢያንስ 15 ሰዎች (ሴቶችን ጨምሮ) በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ከሕግ ውጭ መገደላቸውንና ሌሎች ሁለት ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱን የኢሰመኮ መግለጫ አመልክቷል። 

በምዕራብ ጎጃም ዞን፣ ቋሪት ወረዳ፣ ወይበይኝ ቀበሌ ጥር 6 ቀን 2016 ለወታደራዊ ቅኝት በአካባቢው የተሰማሩ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ቤት ለቤት ባደረጉት አሰሳ 6 ሲቪል ሰዎችን ከየቤታቸው አውጥተው ከሕግ ውጭ እንደገደሏቸው ምስክሮች ለኢሰመኮ አስረድተዋል መባሉን አዲስ ማለዳ ተመልክታለች።

ባለፈው ሳምንት ከአምሥት የሚልቁ ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች እንዲሁም የአሜሪካ መንግስት አዲስ አበባ በሚገኘው አምባሳደሩ በኩል በመራዊ ከተማ በንጹሐን ዜጎች ላይ ግድያ መፈጸሙን እና በገለልተኛ አካል እንዲመረመር መጠይቃቸውን መዘገባችን አይዘነጋም።

Source: Link to the Post

Leave a Reply