ቢጂአይ-ኢትዮጵያ በአሰራሩ፣ በማምረት ሂደቱ እና በስርጭት ሞዴሉ ላይ ለውጥ ለማምጣት ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ሊያደርግ መሆኑን ገለፀ።

ኢንቨስትመንቱ የኩባንያውን ፋብሪካዎች የማምረት አቅም መጨመርን እንዲሁም የአዲስ አበባ ፋብሪካ ሰበታና ማይጨው ወደሚገኙት ሁለቱ የቢራ ፋብሪካዎቹ ማዛወርን ያካትታል ተብሏል።

የቢጂአይ ኢትዮጵያ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሚ/ር ሄርቬ ሚልሃድ በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ “ይህ ኢንቨስትመንት ኩባንያችንን የበለጠ ተወዳዳሪ ለማድረግና ጥራት ያላቸውን ምርቶቹን ለውድ ደንበኞቹ ለማቅረብ ከምንሰራቸው ዋና ዋና ፕሮጀክቶች አንዱ ነው” ብለዋል።

የቢጂአይ-ኢትዮጵያ ስትራቴጅካዊ ለውጥ መተግበር ያስፈለገው ድርጅቱ በኢትዮጵያ ከተፈጠረው የገበያ ለውጥ፣በኢንዱስትሪው ውስጥ ከሚታየው አጠቃላይ ተወዳዳሪነት ጋር እርምጃውን ለማስተካከል፣ እንዲሁም የኩባንያውን እድገት ለማፋጠንና ጠቅላላ አመለካከቱን ለማሻሻል ነው ተብሏል።

ድርጅታቸዉ በኢትዮጵያና በገበያዋ ከፍተኛ አቅም እንዳለ እናምናለን ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚዉ ፤ኢትዮጵያ እያደገችና እየተለወጠች ስትሄድ የገበያውን ፍላጎት ጋር የተጣጣመ አሰራር ለመዘርጋት ተዘጋጅተን ወደ ተግባር ገብተናል በማለት አክለዋል።

በሚቀጥሉት አመታት የማምረት አቅማችንን በእጥፍ በማሳደግ በዓመት ወደ 10 ሚሊዮን ሄክቶ ሊትር ለማድረስ አልመናል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በመካሄድ ላይ ካሉት ዋና ዋና ተግባራት አንዱ በማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ላይ ኢንቨስት በማድረግ የማምረት አቅሙን ማሳደግ ነው ሲሉም ነዉ የገለጹት፡፡

በውሃ አቅርቦት ውስንነትና የሎጂስቲክስ ተግዳሮቶች ምክንያት በአዲስ አበባ የሚገኘውን የቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካን ለማዛወር መገደዳቸዉን ገልጸዋል፡፡

ነገርግን ችግሩ ራሱ የሌሎች ፋብሪካዎቻችንን የማምረት አቅም ለማሳደግ እድል ፈጥሮልናል ሲሉም ዋና ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል።

ቢጂአይ-ኢትዮጵያ ለመተግበር ካቀዳቸው የኢንቨስትመንትና የሰው ሃይል አስተዳደር ማሻሻያ ስራዎች ባሻገር የምርት ስርጭቱን ለማዘመን አዲስ ስትራቴጂ በመቅረፅ ወደ ተግባር ገብቷል።

በምርት ስርጭት ላይ የሚተገበረው ፕሮጀክት የሽያጭ አሰራርን በማዘመን የሽያጭ ሰራተኞችንና ወኪሎች ወደ ደንበኞች የበለጠ ቀርበው እንዲሰሩ ለማስቻል ያለመ ነው ተብሏል።

ቢጂአይ-ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ባሉት ሰባት ፋብሪካዎቹ ለ3ሺህ 5መቶ ቋሚ ሰራተኞች እና ለ2ሺህ ጊዜያዊ ሰራተኞች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡

በእስከዳር ግርማ
ታህሳስ 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply